አጀንዳ ከመቀበል ወደ መስጠት – የውጭ ጫናን ጥሶ የሚወጣው የኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ

10
ዓለም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለሚወስኑ እንጂ በሌሎች ጥላ ሥር ለሚያጎበድዱ ሀገራት ክብር አይሰጥም።
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችበት የታሪክ ምዕራፍ ይህንን እውነት በሚገባ የተገነዘበ ነው። ለዘመናት በኀያላን ሀገራት አጀንዳ ስትቀበል እና የመከላከል ፖለቲካ ስታራምድ የኖረችው ሀገር ዛሬ አጀንዳ ከመቀበል ወጥታ ቀጣናዊ አጀንዳዎችን ወደ መስጠት ልዕልና ተሸጋግራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገሪቱን አዲስ የከፍታ ምዕራፍ እና የማይበገር አቋም በተደጋጋሚ አስረድተዋል። “የኢትዮጵያን መሻት እና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኀይል የለም፤ የጂኦግራፊ እስረኛ እንድንኾን ያደረገን የውስጥ ስንፍናችን እና መከፋፈላችን ነው” በማለት የውጭ ጫናን መመከት የሚቻለው በውስጥ ጥንካሬ ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በድል ማጠናቀቅ እና የቀይ ባሕርን የጂኦ-ፖለቲካ መብት ጥያቄ በድፍረት አደባባይ ማውጣት የዚህ አጀንዳ ሰጪነት ትላልቅ ማሳያዎች ናቸው። ሀገሪቱ የራሷን የብሔራዊ ጥቅም መስመርም በራሷ እጅ እያሰመረች መኾኗን የሚያስረግጥ እርምጃ ነው።
ይሁን እና ኢትዮጵያ ይህንን የከፍታ ጉዞ በምትገፋበት ወቅት ታሪካዊ ጠላቶች እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ራሷን ችላ የፖለቲካ ነጻነቷን እንዳታውጅ እንቅልፍ ያጡ ኀይሎች ዛሬም አሉ።
የጥፋት ኀይሎች በቀጥታ ወታደራዊ ወረራ ሀገሪቱን ማንበርከክ እንደማይችሉ ከታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህም አሁን የሚጠቀሙት ዋነኛ ስልት የውጭ የዲፕሎማሲ ጫናን ማክበድ እና የውስጥ የእርስ በዕርስ ግጭትን በማቀጣጠል የሀገርን ጉልበት ማድከም ነው። ይህንን የተደራረበ የውጭ ጫና እና የጠላት ሤራ ማክሸፍ የሚቻለው በኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ ብቻ ነው።
የውጭ ጠላቶች ኀይላቸው የሚገዝፈው እኛ ስንከፋፈል ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያን ከጥቃቅን የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ልቀው በሀገር
ሉዓላዊነት እና በብሔራዊ ክብር ላይ እንደ አንድ ጠንካራ አለት ሲቆሙ የትኛውም ጫና ተሰባብሮ ይወድቃል።
✍️በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ ታሪክ ማስቀመጫ ሳንዱቁ ጣና።