
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።
በማህበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት በአምስት ዓመታት ውስጥ ቤቶችን ገንብተን ለማስረከብ ለሕዝባችን ቃል ገብተናል፤ ይህንንም ቃላችንን በተግባር ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ያለ እረፍት እየተጋን እንገኛለን ብለዋል።
ሕዝባችን በመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት የሚገጥመውን ፈተናና ስጋት በሚገባ እንረዳለን፤ ደረጃቸውን የጠበቁና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶችን ማመቻቸት የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን፣ ለዜጎቻችን ያለብን አደራና ኃላፊነት መሆኑንም ጠንቅቀን እንገነዘባለን ነው ያሉት።
ዋነኛ ትኩረታችን ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ፣ የሕዝባችንን የመኖሪያ ቤት ጫና ማቃለል እና በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ቤተሰቦች የተሻለ የኑሮ ምዕራፍ መክፈት መኾኑን አመላክተዋል።
