
የቴክኖሎጂ ለውጥ የዘመናዊ ዓለምን አቅጣጫ በመቀየር የኢኮኖሚ ዕድገትን እያረጋገጠ ይገኛል። የሀገር ደኅንነት መጠበቂያ ዋነኛ አካልም ኾኗል።
ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂን ከልማት ጋር በማስተሳሰር የዲጂታል ሽግግሯን ለማፋጠን የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነች ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዚህ ዲጂታል ጉዞ ጠንካራ መሠረት ጥሎ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ወደ ትግበራ አስገብታለች።
ለሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI)፣ ለዳታ ሳይንስ፣ ለዲጂታል ክህሎት ግንባታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የሰባት ሚሊዮን የኮደርስ ሥልጠና እና የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደግሞ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ እያፋጠኑ ነው።
ለቴክኖሎጂ በተሰጠው ትኩረት በ2018 በጀት ዓመት በኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች ቁጥር ወደ 91 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማሳደግ፣ የኔትወርክ ሽፋንን 99 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ፣ የ4ጂ የኔትወርክ ሽፋንን ከ82 ነጥብ 2 በመቶ በላይ ማድረስ፣ የ5ጂ ኔትወርክን በበርካታ ከተሞች ማድረስ ተችሏል።
በቴሌ ብር 60 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት ከ9 ነጥብ 13 ትሪሊዮን ብር በላይ ማስተናገድ መቻሉን የተቋሙ መረጃ ያመለክታል። ወጣቶች ሁሉን አቀፍ ዕውቀት እንዲኖራቸው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠናን በማጠናቀቅ ወደ ሰባት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና ተሸጋግሯል። ከ40 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ኾነዋል።
በፋይናንስ ዘርፍ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች የዜጎችን የዕለት ተዕለት ግብይት አቅልለዋል። የቴክኖሎጂ ስታርታፖች መበራከት ለወጣቱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተቋማት የተጀመረው የቴክኖሎጂ የለውጥ ሪፎርም አገልግሎትን ቀልጣፋ አድርገዋል፤ ተደራሽነትንም አስፍተዋል።
የሳይበር ደኅንነት መጠበቅ የብሔራዊ ደኅንነት ዋነኛ አካል በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዲጂታል መሠረተ ልማት አውታር መስፋፋት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ አማካይ የኢኮኖሚ ምጣኔ በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ ጉልህ ሚና ማበርክታቸውንም ተናግረዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን ጥራት እና ተደራሽነት በማሳለጥ በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።
የዲጂታል ሥነ ምህዳርን ለመፍጠር የሚያስችሉ የሕግ እና የፖሊስ ማዕቀፎች ወደ ሥራ ገብተዋልም ነው ያሉት።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!![]()
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
