ከወደብ ኪራይ ጥገኝነት ወደ አፍሪካ በርነት የሚያሸጋግረው የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ!

21

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባሕር በሯን ባጣችባቸው 36 ዓመታት 72 ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ ከፍላለች።

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ማጣቷ በዓለም አቀፍ ንግድ ሂደት ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንድትከፍል፣ በዓለም የንግድ መስመር ተወዳዳሪ እንዳትኾን እንዲሁም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይኖራት አድርጓታል።

የባሕር በር አልባነት ጉዳዩ ከኢኮኖሚ ባሻገር የጂኦ-ፖለቲካዊ ደኅንነት እና የህልውና ዋስትና ጉዳይ ነው። የባሕር በር ማጣት ኢትዮጵያ ለስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ተጋላጭ ከማድረጉም በላይ ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎችን ያስከትላል።

የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ተመራማሪ ሰለሞን ተፈራ ከመገናኛ ብዙኀን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመኾኗ የገቢ እና የውጪ ንግድን ለማካሄድ ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ትከፍላለች፤ ባለፉት 36 ዓመታትም 72 ቢሊዮን ዶላር ከፍላለች ብለዋል፡፡

ይህም ሕዳሴ ግድብን ለመገንባት ከወጣው ወጪ አንጻር ሲታይ ሀገሪቱ ባለፉት 36 ዓመታት ለጅቡቲ የወደብ ኪራይ ያወጣችው ዶላር ቢሰላ ከ12 በላይ የሕዳሴ ግድቦችን ማሠራት የሚያስችል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የከፈለችው 72 ቢሊዮን ዶላር ሀገር ውስጥ ኢንቨስት ቢደረግ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ይበልጥ ያረጋግጥ ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለባሕር በር የምትከፍለው ዓመታዊ ኪራይ እና ወደብ አልባ መኾኗ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያደረሰባት ነው፤ የባሕር በር አልባ መኾኗ እያስከተለባት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታት የጀመረችው ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ይህንን እውነት በመረዳት የሀገሪቱ መሪዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት በተደጋጋሚ አንስተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያን የደኅንነት እና የልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። ጉዳዩ የትውልድ አደራ እና የፍትሕ ጥያቄ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና በትብብር መርህ ላይ የተመሠረተ መኾኑን አስገንዘበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በበኩላቸው የባሕር በር ማግኘት ግዙፍ ለኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢኮኖሚ ደኅንነት እና የዕድገት እኩል ተጠቃሚነት ወሳኝ መኾኑን በግልጽ አስምረውበታል። ኢትዮጵያ ያላት የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የሰላም አስተዋጽኦ እና በጋራ የመልማት ፍላጎትን በመረዳት ፍትሐዊ በኾነ መልኩ የባሕር በር ባለቤት መኾን እንዳለባት ጽኑ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

የባሕር በር ፍላጎት የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይኾን የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ታሪካዊ አጀንዳም ነው።

ይህንን ብሔራዊ እና ታሪካዊ ሐቅ በመገንዘብ ኢትዮጵያውያን ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የሐሳብ እና የብሔር ልዩነት ወጥተው ለሀገራቸው ቀጣናዊ ደኅንነት እና ብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ መቆም እንዳለባቸው ተመላክቷል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_04_2019_ዓ_ም

✍️:-ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

Previous article‎የሉዓላዊነት አዲስ መልክ፦ ከአረንጓዴ አሻራ እስከ ሀገራዊ ህልውና
Next articleበሀገራችን ከ9 ነጥብ 13 ትሪሊዮን ብር በላይ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲዘዋወር ያገዘው የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ።