
በአማራ ክልል የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር በበርካታ አካባቢዎች እና ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህም ተጠቃሚ የኾኑ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳዳርም ምገባ ከተጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ በዚህ የምገባ መርሐግብር ተጠቃሚ ከኾኑ አካባቢዎች መካካል የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር አንዱ ነው። በምገባው ልጆቻቸው ተጠቃሚ ከኾኑ ወላጆች መካከል አቶ ወሌ ንጉሴ እና ወይዘሮ ይደምቃል ጓዴ ለአሚኮ እንደገለጹት በትምህርት ቤቱ ምገባ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው እና አቅም ለሌላቸው ወላጆች ትልቅ እፎይታን የሰጠ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የምገባ ሥርዓቱ እንዳይቋረጥም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ምገባው ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ ስለማገዙም ነው የተናገሩት
በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካካል የአንድነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ካሰች አምላኬ እና የባሁንኩ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ አንደኛ ክፍል መምህር ጌትነት መሠረት እንገለጹት ምገባ ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደሚቸገሩ እና እንደሚያቋርጡ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ ምገባ ከተጀመረ ወዲህ ግን ትምህርታቸውን በአግባቡ ከመከታተላቸው በተጨማሪ የሚያቋርጡ ተማሪዎች መቀነሱንም ገልጸዋል፡፡ የተማሪዎች የትምህርት የመከታተል ፍላጎታቸው ላይም መሻሻል መታየቱን ነው የገለጹት፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ወንድማገኝ ማኔ በአሥተዳደሩ በተለይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስፋት የምገባ ሥርዓት እየተካሄደ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ምገባውን ለማስቀጠልም ዕቅድ ስለመያዙ ነው ያብራሩት፡፡
እስከአሁን ድረስ ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ እንደኾኑ የገለጹት አቶ ወንድማገኝ ከ57በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሐግብሩን እያስኬዱት ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ ምገባ በመጀመሩ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ምገባ ለተማሪዎች የነገ ተስፋቸው መሠረት ጭምር ነው ያሉት ምክት ኀላፊው የምገባ መርሐግብሩ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመኾኑ ወላጆች፣ ባለሀብቶች እና አጋር አካላት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሐሳብ እንዲያግዙም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ በክልሉ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ በ86 ወረዳዎች በሚገኙ 358 ቅድመ-አንደኛ እንዲሁም 801 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 364 ሺህ 79 ተማሪዎችን በመመገብ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ መቻሉን ነው ያብራሩት።
የተገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግም በሁለተኛው ሩብ ዓመት በአብዛኞቹ የክልሉ ወረዳዎች የተማሪዎች ምገባ መርሐግብሩ በስፋት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ:-ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
