🌴 ባሕር ዳር የተፈጥሮ ስጦታዋን ከዘመናዊ አቅም ጋር አዋሕዳ ለዓለም አቀፍ መድረኮች ተመራጭ ኾናለች።

12

 

በባለ ግርማ ሞገሱ ጣና ሐይቅ እና የበርካታ ሀገሮች ዓይን ማረፊያ በኾነው ዓባይ ወንዝ ዳርቻ የምትገኘው ባሕር ዳር ከተማ የተፈጥሮ ስጦታዋን ከአደገ የዘመናዊነት አቅም ጋር አዋሕዳ ለዓለም አቀፍ መድረኮች ተመራጭ ከተማ በመኾን ጎልታ እየወጣች ትገኛለች።

ዘንድሮም በጥቅምት አጋማሽ የሚደረገውን 12ኛውን የጣና ፎረም ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ናት።

ባለፉት ዓመታትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ስብሰባዎችን፣ ጉባኤዎችን እና ፍልስፍናዊ እና ፖለቲካዊ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ ልምዷን አዳብራለች። ተፈጥሮ ከለገሰቻት ጸጋ ባሻገር ደረጃቸውን የጠበቁ ባለኮከብ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሰፋፊ እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አውታር የተገጠመላቸው የኮንፈረንስ አዳራሾች በከተማዋ መገንባታቸው ተመራጭ አድርጓታል። በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል አቅምም ፈጥራለች።

ቀልብን የሚስብ ውበቷ እና ጽዳቷ፣ ከተማዋ የምትታወቅበት የማይደበዝዝ ሰላማዊ እና ሞቅ ያለ የእንግዳ አቀባበል ባሕል ዓለም አቀፍ ተወካዮችን እና ዲፕሎማቶችን ቀልብ የሚስብ ነው። በቅርቡ ደረጃውን ከፍ ያደረገው ደጅአዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደግሞ በአንድ ቀን በርካታ ቁጥር ያላቸውን በረራዎች በማስተናገድ እንግዶችን በምቾት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ለማስቻል ትልቅ እድል ፈጥሮላታል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ የአፍሪካ መሪዎች እና ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚሳተፉበትን ዓለም አቀፍ የጣና ፎረም ለማስተናገድ ሙሉ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ገልጸዋል።

ከተማዋ ቀደም ሲል ከነበሩት የኮንፈረንስ ዝግጅቶች ትምህርት በመውሰድ በዘንድሮው ፎረም ላይ በርካታ አዲስ እና ልዩ ዝግጅቶችን ማድረጓንም ጠቅሰዋል።

ከተማዋ ሙሉ በሙሉ የሰላም እና የደኅንነት ድባብ እንዲኖራት ተደርጎ አስተማማኝ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

ለፎረሙ ውይይቶች ምቹ የኾኑ በጣና ሐይቅ ዳርቻ የተገነቡ ዘመናዊ ሪዞርቶች ዝግጁ እንደኾኑም አንስተዋል። እንግዶች በሐይቁ ላይ በፈጣን ጀልባዎች በደቂቃዎች ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸ መኾኑንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት፣ የብስክሌት መስመሮች እና ተጨማሪ የመዝናኛ ፓርኮች ለሙሉ አገልግሎት እንደበቁም አመላክተዋል።

ከዚህ ባሻገር የአማራ ክልልን እና የኢትዮጵያን ባሕል የሚያስተዋውቁ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች፣ ከአምራች እና ሻጮች ጋር በመነጋገር የሀገር ውስጥ የስጦታ ዕቃዎች እና የቱሪዝም ምርቶች ለገብያ እና ለዕይታ መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።

ይህ ጉባኤ የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ፍሰትን በማሳደግ ለከተማዋ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ ነው የተናገሩት።

የከተማዋ ማኀበረሰብ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተለመደውን የላቀ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየአካል ጉዳተኞችን የትራንስፖርት እንግልት ያቃለለው ሥራ!