
እውነተኛ ማንነታችን እና አቅማችን የሚለካው ባለን አካላዊ ሁኔታ ብቻ ሳይኾን ባለን አመለካከት፤ ባልተሰበረው መንፈሳችን እና ለዓላማችን ባለን ቁርጠኝነት ነው።
በሕይወት መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና እንቅፋቶች ሊያዘገዩን ይችላሉ፤ ነገር ግን በፍጹም ሊያስቆሙን አይችሉም ይላሉ ሥራ ፈጣሪው ሀሰን ይማም።
ለአካል ጉዳተኞች የትራንስፖርት እጥረት እና እንግልት ትልቅ ራስ ምታት ኾኖ ያለ እንቅፋት ነው። ይህንን ማኅበራዊ ችግር የተገነዘቡት አቶ ሀሰን ይማም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። እኒህ የፈጠራ ሰው የሠሩት ተግባር ዛሬ ላይ በርካታ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
አቶ ሀሰን ይማም ከዚህ ቀደም የገጠማቸውን የትራንስፖርት ችግር እና አደጋ በማስታወስ፣ ከጉዳታቸው ሲያገግሙ ግን እንዲሁ ዝም ብለው ቁጭ አላሉም። ይልቁንም አካል ጉዳተኞች መደበኛ የሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶችን ሲጠቀሙ የሚያጋጥማቸውን የሚዛን መዛባት እና የፍሬን ችግር ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችል አስደናቂ የሞተር ማሻሻያ አድርገዋል።
በሁለት እግር ሞተሮች በሁለት ጎማዎች ላይ ሚዛን ጠብቆ ለመቆም የሚከብዳቸውን የአካል ጉዳተኞች ችግርን በማስወገድ በሦሥት እግር የተዋቀረ እና የተሻሻለ ሥርዓት የተገጠመለት ሞተር በመሥራት ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ያለ ስጋት እንዲያሽከረክር መፍትሔ ዘይደዋል።
ተጠቃሚዎች በሦስት እግር በተዋቀረውው ሞተር ሳይክል የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን፤ የንግድ ሥራዎቻቸውን እና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ያለአንዳች እንግልት እና ያለሰዎች እርዳታ በራሳቸው አቅም መፈጸም መቻላቸውን ገልጸዋል።
ይህ ፈጠራ አካል ጉዳተኞች በከተማ ውስጥ በፈለጉት ሰዓት እና ቦታ ተንቀሳቅሰው ሕይወታቸውን እንዲመሩ ከፍተኛ እፎይታንም ሰጥቷል።
አቶ ሀሰን ወደፊት ይህንን ፈጠራ በኤሌክትሪክ ጭምር በማስፋፋት ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን ድጋፍ ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ ህልም አላቸው።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ሰመሃል ፍስሐ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
