አዳኝ ክንፍ!

37

 

የዘመናችን ውጊያ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ነው። የኢትዮጵያ አየር ኃይልም የትናንት ጀግንነቱን ከዛሬው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም ጋር በማቀናጀት የኢትዮጵያን ሰማይ በአስተማማኝ ሁኔታ እየጠበቀ ይገኛል። ለሀገር አለኝታነቱንም እያስመሰከረ ዘመናትን ተሻግሯል።

አየር ኃይሉ ከሀገሪቱ የነጻነት እና የሉዓላዊነት ታሪክ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። የጽናት እና የጀግንነት ተምሳሌት ስለመኾኑም ይነገርለታል። ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን የአየር ክልል እያስከበረ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኃይል ሚዛን እና የጸጥታ ዋስትና በመኾን የጎላ ሚናውን ተጫውቷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ በጀግንነት የተቃኘ፣ በሙያዊ ብቃት የተቀረጸ፤ በተምሳሌትነት የሚጠራ፣ ለጠላት ራስ ምትሃት፣ ለሀገር ዘብ ነው። በታሪኩም በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ላይ ያሳየው የበላይነት ተቋሙ ለሀገር ሰላም እና ደኅንነት የከፈለውን ዋጋ ያመላክታል።

በአሁኑ ወቅት የአየር ኃይሉ አቅሙን አጎልብቶ ለማንኛውም ድንገተኛ ጥቃት ወይም ስጋት በደቂቃዎች ውስጥ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ዝግጁነትን ገንብቷል። በከፍተኛ የሥነ ልቦና ልዕልና፣ በበሰለ ሙያዊ ብቃት እና በማይወላወል ሀገራዊ ፍቅር የተገነባው አየር ኀይሉ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የሰላም ዘብ ኾኖ ይቀጥላል።

የኢፌዴሪ አየር ኀይል ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኀይሉ በምስረታው በአፍሪካ ቀዳሚ ስለመኾኑ ይገልጻሉ። በዘመኑም የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለዛሬው ትውልድ በጽናት እንደበቃም አመላክተዋል።

የዚህ ዘመን ውጊያ በመሬት ምሽግ በመቆፈር፣ መድፍ እና ታንክ በማሰለፍ የሚደረግ ሳይኾን በቴክኖሎጂ የሚከናወን ነው ብለዋል። ይህንን መሠረት ተደርጎ ተቋሙ በሰው ኀይል ግንባታ፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ፣ የውጊያ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት፣ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ኢትዮጵያን የሚመጥን አየር ኀይል ስለመገንባቱ አብራርተዋል።

መንግሥት በሚሠጠው አቅጣጫ መሠረትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አየር ኀይሉ ሁሌም ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአትዳፈሩት፤ ጠላት የማይሻገረው የእሳት አጥር ነውና!
Next articleየአካል ጉዳተኞችን የትራንስፖርት እንግልት ያቃለለው ሥራ!