
የባሕር ኀይላችን መልህቅ የጣለበት፣
የኢትዮጵያ ወጣቶች ዋና የዋኙበት፣
የት አለ ባሕሩ በደም የማልንበት።
ይህ ግጥም ስንኝ ብቻ አይደለም፤ ቁጭት የወለደው የምሬት ቃል እንጅ። ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሤራ ከቀይ ባሕር ስትገለል እና የባሕር ኀይሏ ሲበተን ነበር ይህ ስንኝ በቁጭት የተጻፈው።
የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ግንኙነት የቅርብ ጊዜ አጀንዳ ሳይኾን የጥንታዊ ሥልጣኔዋ፣ የንግዷ እና የሉዓላዊነቷ ዋነኛ ምሶሶ ኾኖ የቆየ ታሪካዊ ሐቋ ነው።
ኢትዮጵያ በአዱሊስ፣ በአሰብ፣ በምጽዋ እና በሌሎች ወደቦች በኩል ቀይ ባሕርን ትቆጣጠር ነበር። የአፍሪካ አርኪኦሎጂ ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊሊፕሰን “ፋውንዴሽን ኦፍ አን አፍሪካ ሲቪላይዜሽን” በተሰኘው መጽሐፋቸው የአክሱም ሥልጣኔ በቀይ ባሕር ንግድ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከሜዲትራኒያን ጋር ጥብቅ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ትሥሥር እንደነበራትም የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ።
ያዕቆብ ኀይለ ማርያም(ዶ.ር) “አሰብ የማን ናት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ኮስሞስ የተባለውን “የክርስቲያን ፎቶግራፊ” መጽሐፍ ጸሐፊ ዋቢ አድርገው በመጥቀስ ንጉሠ ነገሥት አጼ ካሌብ በወቅቱ የዳበረ የባሕር ኀይል እንደነበራቸው እና ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመንን እና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበር አትተዋል።
የአክሱም፣ የዛግዌ፣ የጎንደር፣ የዘመነ መሳፍንት እና ሌሎች መንግሥታት መቀያየር ኢትዮጵያን የባሕር በር አላሳጣትም ነበር። ኾኖም በቅርቡ በተፈጠረ የታሪክ እጥፋት በፖለቲካ ሤራ ትውልዱ ቀይ ባሕርን እንዲያጣ፣ ስለ ባሕር በር እንዳያነሳ ሢሠራ ቆይቷል።
በዚህም ለወደብ ኪራይ ቢሊዮን ዶላርን እንድትከፍል ተገድዳለች። ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ገንዘብ የበርካታ መሠረተ ልማቶችን በር ዘግቷል፣ የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ፈጥሯል፣ የወጣቶችን የሥራ ዕድል አምክኗል። ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷንም ተፈታትኗል።
አሁን ላይ ግን ቀይ ባሕር እናቱን ናፍቋል፣ ኢትዮጵያም ታሪካዊ ልጇን ፈልጋለች። በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ የምታምነው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት ጥረት እያደረገች ነው። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያን እውነታ ተርድቶ ከጎኗ ቁሟል።
ቀይ ባሕርን የናፈቀው የባሕር ኀይሏ ድጋሜ ተቋቁሟል፤ የቀጣናው የሰላም ዋስትና የመከላከያ ሠራዊቷ ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ ታጥቆ የምሥራቅ አፍሪካን ደኅንነት ሊያስጠብቅ በጽናት ቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተዘጋጀንባቸው ዘመናት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲተራኒያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል፤ ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልም እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
