
በአማራ ክልል ብቁ እና ተወዳዳሪ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሞዴል ትምህርት ቤቶች በመንግሥት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየተገነቡ ይገኛሉ።
በክልሉ ግንባታቸው ከተጀመሩ ሞዴል ትምህርት ቤቶች መካከል በሰሜን ሽዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ የሚገኘው የአላላ ሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት አንዱ ነው።
የአላላ አማን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሞገስ ማሞ በአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ልጆቻቸውን ወደ ወረዳው መቀመጫ ከተማ እየላኩ ሲያስተምሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የቤት ኪራይ እና የትራንስፖርት ወጪ መሸፈን የማይችሉ ተማሪዎች ደግሞ 8ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ይገደዳሉ።
በዚህም ምክንያት በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባላቸው ለረጅም ዓመታት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ይሁን እንጅ አሁን በቀበሌያቸው የሚገነባው የሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ልጆቻቸው ያለምንም ወጪ እና እንግልት እንዲማሩ ትልቅ ዕድል
እንደሚፈጥርላቸውም በደስታ ገልጸዋል።
የአላላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ መቅደስ ንጉሥ እና ተማሪ ናትናኤል መኮንን በወረዳው ከተማ ለመማር የሚጠይቀው የሦሥት ሰዓት የእግር ጉዞ አድካሚ መኾኑን አንስተዋል።
አሁን ላይ በቀበሌያቸው እየተገነባ ያለው አዲስ የሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለስጋት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ኾነው እንዲማሩ ትልቅ ተስፋ እና መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የሰሜን ሽዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዋሲሁን ብርሃኑ አሁን ላይ የአላላ ሁለተኛ ደረጃ ሞዴል ትምህርት ቤት አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 76 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። እስካሁን የመማሪያ እና የአሥተዳደር ክፍሎችን ጨምሮ 28 ብሎኮች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ግንባታው በማኅበረሰቡ ጠንካራ ድጋፍ ታግዞ በዚህ ዓመት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ከወዲሁ ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም አቶ ዋሲሁን ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ በዞኑ ለሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም አርአያ እንደሚኾን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ትምህርት ቤቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ለአሚኮ ገልጸዋል።
ሞዴል ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች ሙሉ ቀን እንዲማሩ የሚያስችሉ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች፣ ብቁ መምህራን እና አስፈላጊ ዘመናዊ የትምህርት ግብዓቶች የሚሟሉላቸው ናቸው ብለዋል።
በተለይም በአካባቢው የሚገኙ የተሻሉ ተማሪዎች እና ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል ያላገኙ ብቁ ተማሪዎችን በመቀበል፣ በቂ ዕውቀት እንዲጨብጡ እና ሀገር የሚገነቡ ውጤታማ ዜጎች ለማፍራት የሚያገለግሉ መኾናቸውን አንስተዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_04_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
