
ጣና ፎረም በየዓመቱ በባሕር ዳር ከተማ የሚካሄድ ትልቅ አህጉራዊ ጉባኤ ነው። አፍሪካውያን መሪዎች ባለፉት ዓመታት 11 ጊዜ በመገናኘት በአፍሪካ ጉዳዮች መክረዋል። ዘንድሮም 12ኛው የጣና ፎረም ሊካሄድ ዝግጅት ተጠናቅቋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ እንደተናገሩት ጉባኤው በአፍሪካ አንገብጋቢ እና ትኩረት በሚሹ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች እንደሚመክር ይጠበቃል። በአህጉሪቱ እየተከሰቱ ለሚገኙት አለመግባባቶች እና ግጭቶች የመፍትሔ ሀሳቦችንም ያቀርባል።
ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ መካሄዱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጎበኙ እድል ይፈጥራል። ከታላላቅ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እስከ ግለሰብ ደረጃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የመፍጠር እድሉም ከፍ ያለ ስለመኾኑ አንስተዋል።
ክልሉ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን የማስተናገድ ብቃቱን የሚያሳይበት ነውም ብለዋል። የማኅበረሰቡን ቱባ የባሕል እና እሴት ለማስተዋወቅ፣ የክልሉን ገጽታ ለመገንባት እና የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማነቃቃት መልካም አጋጣሚ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ይህ መድረክ ከጉባኤው ባለፈ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በተግባር የሚታይበት በመኾኑ ይህንኑ አስቦ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ይህንን መሠረት አድርገው ሆቴሎች እና የመስተንግዶ ተቋማት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህ የአማራን ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያን መልካም ስም እና ገጽታ ለዓለም የምናሳይበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ሁሉም የባሕር ዳር እና አካባቢው ሕዝብ ጉባኤውን ስኬታማ ለማድረግ እንደወትሮው ሁሉ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እንዲወጣም ቢሮ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
