🕊️ ከመሣሪያ አፈሙዝ ወደ ጠረጴዛ – የዘመኑ የጀግንነት መገለጫ

69

 

የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ዕውን ሊኾን የሚችለው ከውጭ በሚመጣ ተአምር ሳይኾን በእኛው በገዛ ልጆቿ እጅ ላይ ነው፤ በተለይም የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውን በመሣሪያ አፈሙዝ ለማስመለስ ጫካ በገቡት ወገኖች ላይ የተመሠረተ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንዳሉት ጦርነት አፍራሽ እንጂ ገምቢ ሊኾን አይችልም፤ በመገዳደል ውስጥ አሸናፊ የለም እና ሀገር ትፈርሳለች እንጂ ሌላ አንዳችም ፖለቲካዊ ትርፍ አያመጣም።

የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠመንጃ ኀይል ለመፍታት መሞከር የገዛ እናትን ደረት በጦር እንደመውጋት የሚቆጠር የታሪክ ስህተት ነው። በተጨማሪም የሕዝብን መከራ ከማራዘም አልፎ ሀገርን ለታሪካዊ ጠላቶች ሤራ ተጋላጭ ያደርጋል።

በእውነተኛ ጀግንነት እና በጭፍን እልህ መካከል ትልቅ ልዩነት አለና የዘመናችን እውነተኛ ጀግንነት ወንድምን በመግደል እና መሠረተ ልማቶችን በማውደም የሚረጋገጥ አይደለም። ይልቁንም ያነገቡትን የጥፋት መሣሪያ ወደ ጎን በመተው ቂም እና በቀልን አሸንፎ ለሰላም ውይይት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ነው።

የታጠቁ ኀይሎች የሰላምን በር እንዲያንኳኩ የሚደረገው ጥሪ የሀገርን ሕልውና እና የንጹሐንን ሕይወት የመታደግ የሞራል ግዴታ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ በተወለደባት ምድር ላይ የሚተኮስ ጥይት ኢትዮጵያን ለማዳከም ሌሊት ከቀን ለሚሠሩ የውጭ ጠላቶች የድል ብሥራት ነውና።

የውስጥ አለመረጋጋቱ ለባዕድ ኀይሎች ክፍተት ስለሚፈጥር ዛሬ ግብጽ እና ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የጥፋት ፍላጎት ለማምከን ብቸኛው መሣሪያ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ነው።

የታጠቁ ኀይሎች የኢትዮጵያ የሰላም ቁልፍ የውጭ አደራዳሪዎች ኪስ ውስጥ ሳይኾን በራሳቸው እጅ ላይ መኾኑን በመገንዘብ የሰላም ጥሪን ተቀብሎ ወደ ጠረጴዛ መምጣት ይገባቸዋል።

ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በሰላማዊ፣ በሠለጠነ እና አሳታፊ በኾነ ሀገራዊ የውይይት መድረክ ላይ ማቅረብ ብቸኛው የሕልውና ዋስትናም ነው።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአንድ ወቅት እንዳሉት “ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካ እናት ናት፤ እናት ሰላም ካላገኘች ቤተሰቡ ሰላም ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ የአህጉሪቱ ሰላምም ከኢትዮጵያ መረጋጋት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።”

ሰላማዊ፣ የተረጋጋች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ለአጠቃላይ የአፍሪካ የጋራ ብልጽግና እና ተስፋ መሠረት መኾኑንም አረጋግጠዋል።

አሁን ጊዜው የባዕዳንን ሴራ ለመቅደድ፣ የሀገርን በር ከጠላት ለመጠበቅ እና ሉዓላዊነትን በጋራ ለማስጠበቅ የጥፋት እና የመጠፋፋት መሣሪያን ጥሎ ለነገዋ ከፍ ያለች ኢትዮጵያ ግንባታ በአንድነት የምንሰለፍበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#አሚኮ #PeaceForEthiopia #Unity #EthiopiaPrevails

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleእርሷን የነኳት ተዋርደዋል፤ እርሷን የነኳት ወድቀዋል!
Next article“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተችው አስተዋጽዖ ምትክ የለሽ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነáˆ