እርሷን የነኳት ተዋርደዋል፤ እርሷን የነኳት ወድቀዋል!

6

 

ኢትዮጵያን አትንኳት፤ መከፋቷ የሚከፋቸው፣ መነካቷ የሚያማቸው፣ እንቅልፍ የሚነሳቸው ልጆች አሏት። ኢትዮጵያን አትንኳት ለክብሯ ደም የሚያፈስሱላት፣ አጥንት የሚከሰክሱላት፣ ሕይወት የሚገብሩላት ልጆች አሏት፡፡ ኢትዮጵያን አትንኳት ቁጣዋ ይጥላችኋል፣ ሰይፏ ይቀላችኋል፣ ማዕበሏ ይውጣችኋል፣ ክንዷ ያደቅቃችኋል፡፡

ኢትዮጵያን አትንኳት ከሕይወታቸው የሚያስበልጧት፣ ከማንም ከምንም በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጓት፣ አጥር ኾነው ዙሪያ ገባውን የሚጠብቋት፣ መሠረት ኾነው የሚያጸኗት፣ ምሰሶ ኾነው የሚያቆሟት፣ ማገር ኾነው የሚደግፏት፣ መከራ የማያስቆማቸው፣ ጨለማ የማይበግራቸው፣ ቸነፈር የማይገታቸው፣ ውሽንፍር የማያስደነብራቸው፣ ነጎድጓድ የማያስደነግጣቸው ልጆች አሏት፡፡

ኢትዮጵያን ስትነኳት ልጆቿ እንደ ነብር ይቆጣሉ፣ እንደ እሳት ይፋጃሉ፣ እንደ ማዕበል ያደባልቃሉ፣ እንደ መብረቅ ያደርቃሉ፣ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ተዋት፣ ኢትዮጵያን ከልጆቿ በላይ እናውቅልሻለን አትበሏት፣ በራሷ ጉዳይ አትግቡባት፣ እርሷ ከራሷም አልፋ ለሌሎች ምልክት እና ምሳሌ የኾነች ናትና።

ኢትዮጵያን አትንኳት የጥቁር ዘር ሁሉ ብርሃን ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የአሸናፊነት ተምሳሌት ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የሥልጣኔ በር ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት የአጥቢያ ኮኮብ ናት፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ምስክር ናት። እርሷን የነኳት አልቀዋል፣ እርሷን የነኳት ወድቀዋል፣ እርሷን የነኳት አፈር ትቢያ ኾነዋል፡፡

ታሪኳን አይተው ይቀኑባታል፣ እሴቷን አይተው ይመቀኟታል፣ ጽናቷን አይተው ይገረሙባታል፣ ሃይማኖቷን አይተው ይደመሙባታል፡፡ የጠበቀ ሃይማኖት የጠበቃት፣ የከበረ ጀግንነት ያስከበራት፣ የጸና አንድነት ያጸናት፣ ረቂቅ የኾነ ብልሃት ያረቃቃት ናትና በአሻገር የሚያዩዋት ሁሉ ይቀኑባታል፡፡

ዘመን አንስቷቸው፣ ጊዜ ደግፏቸው ጉልበት ያገኙት ሁሉ የክፋት ዐይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ይጥላሉ፣ መክረው ዘክረው ጦር ያዘምታሉ፡፡ ድንበሯን አልፈው የሚፈልጉትን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ማድረግ ያስባሉ፣ ይመኛሉ፡፡ እርሷ በረዘመ የታሪክ ጉዞዋ ያለ ጠላት ውላ አታድርም፤ ጠላቶች ይመክሩባታል፣ ይዘክሩባታል፣ በምን እንደሚያጠፏት፣ በምን እንደሚያሳንሷት፣ በምን ከታሪክ መዝገብ ላይ እንደሚፍቋት ይዶልቱባታል፡፡

የበዙ ጦርነቶች ታወጁባት ሁሉንም አሸነፈቻቸው፣ የበዙ ጠላቶች ተነሱባት ሁሉንም ጣለቻቸው፡፡ እያሸነፈች ትገሰግሳለች፣ እያሸነፈች በታሪክ መዝገብ ላይ ከፍ ከፍ ትላለች እንጂ ጠላቶቿ ዝም ብለው አይተኙም። ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከሚነሱባት ጠላቶቿ ላይ ከድል ላይ ድል እየደራረበች ትቀጥላለች፡፡

ጠላቶች በቀደመው ዘመን ዘመናዊ ሠራዊት አስታጥቀው፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ነገሥታቱ፣ ወይዛዝርቱ እና ጎበዛዝቱ በአደባባይ ወጥተው፣ ሂዱ ያችን ሀገር ውጓት፣ በእኛ ሥርም አድርጓት ብለው መርቀው ይልኳቸው ነበር፡፡ ሠራዊታቸውም መልካም ምኞቱን ተቀብሎ ባሕር እየከፈለ፣ የብስ እያቋረጠ ይመጣል፡፡ የሸኙት ነገሥታት ሠራዊታቸው ድል እንደሚቀዳጅ በሙሉ ልብ ያምናሉ፣ በቅንጡው ቤተ መንግሥታቸው ተቀምጠው የድል ዜናውን ይጠባበቃሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ሠማይ ሥር የሚሰማው ግን እንደጠበቁት አይኾንላቸውም፣ የላኩት ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ክንድ ተመትቶ፣ በሰይፋቸው ተቀልቶ፣ በጎራዴያቸው ተበልቶ፣ በሳንጃቸው ተወግቶ እንዳልነበር ይኾናል፡፡ በደስታ የላኩት ወይዛዝርት በሐዘን ያለቅሳሉ፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ፣ ነገሥታቱ አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡ ምነው በቀረብን ሲሉ ይጸጸታሉ፡፡

ኢትዮጵያ በግፍ የመጣባትን መቅጣት፣ በትዕቢት የነካትን መምታት ታውቅበታለችና፣ የሚነኳትን ስታሳፍራቸው፣ የሚደፍሯትን ስታጠፋቸው ኖራለች፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ቀደመው ዘመን ሁሉ ዛሬም ጠላቶቿ ተነስተውባታል፡፡ ጠላቶቿ የበረከቱ ናቸው፡፡ ገሚሶቹ በጉያዋ ተወሽቀው ያደሟታል፣ ይወጓታል፡፡ ገሚሶቹ በባሕር ማዶ ኾነው በጉያዋ ተወሽቀው የሚወጓትን ያበረታሉ፣ የኢትዮጵያን እውነት እያዳፈኑ የጠላቶቿን ሐሰት ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ በጉያዋ የተወሸቁት ቡድኖች ሲሸነፉባቸው በአሻገር ያሉት ላኪዎቻቸው ዋይታ ያበዛሉ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያበዛሉ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ይታትራሉ።

በዚህ ዘመን የሚነሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደ ቀደመው ሁሉ ራሳቸው መጥተው ውጊያ አይከፍቱም፣ ራሳቸው መጥተው በኢትዮጵያ ተራራዎች እና ኮረብታዎች አይሞቱም፡፡ የዚህ ዘመን ጠላቶች በአሻገር ኾነው ዱላ እያቀበሉ በጉያዋ የተወሸቁ ባንዳዎችን ያበረታታሉ ይደግፋሉ እንጂ።

ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሀገራቸውን ሳያስደፍሩ የኖሩት ኢትዮጵያውያን ታዲያ በዘመኑ ለተነሳባቸው ጠላትም ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ በጦርነት የመጣውን በጦርነት፣ በሐሰት የመጣውን በእውነት ድል ይመቱታል እንጂ።

ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነቷ ኖራለች። ወደፊትም ትኖራለች ይላሉ። የኢትዮጵያ ሕልውና ታሪክ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ጸና ቆይቷል። በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ቢነሱም ሁሉም በኢትዮጵያውያን ክንድ እየተመቱ ወደመጡበት ተመልሰዋል ነው የሚሉት።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ የኖረችው በልጆቿ ደም ነው፤ የልጆቿ ደም አጽንቷት፣ ጠብቋት እና አስከብሯት ኖሯል። እነሆ ዛሬም እንዳስከበራት እና እንዳጸናት ነው።

አዲሱ ትውልድ የሀገሩን ነጻነት እና አንድነት ለመጠበቅ ሁለት አፎት ያለው ሠይፍ ጨብጦ መዋጋት የኖርበታል፤ በአንድ ወገን ከውስጥ ልዩነት በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ ጠላቶች ነው የሚሉት።

ላትችሏት አትንኳት፣ ላትጥሏት አትግፏት እርሷ ጸንታ የኖረች፣ መሠረቷን አለት ላይ ያጸናች ጽኑ ናትና።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_03_2019_ዓ_ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሰው ሰራሽ አስተውሎት ለሀሰተኛ መረጃ መስፋፋት እንዴት ምቹ ኾነ?
Next article🕊️ ከመሣሪያ አፈሙዝ ወደ ጠረጴዛ – የዘመኑ የጀግንነት መገለጫ