
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም በጥናት እና ምርምር በመደገፍ በዘላቂነት ለማስጠበቅ ያለመው የናይል እና ቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ ፎረም በይፋ ተመስርቶ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
የፎረሙን መመስረት አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ፎረሙ በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በ32 መሥራች አባላት ተደራጅቶ ሥራውን በይፋ ጀምሯል ሲሉ የፎረሙ ዋና ሠብሣቢ አበበ ገመቹ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የናይል እና የቀይ ባሕር ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው የሚል ትውልድን በመፍጠር ናይል እና ቀይ ባሕርን በተመለከተ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅሞች በዲፕሎማሲ እና በሕጋዊ መንገድ በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጥናት እና ምርምር መደገፍ ዋና የፎረሙ ዓላማ ነው ያሉት ደግሞ የፎረሙ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሰለሞን ተፈራ ናቸው።
ፎረሙ የባሕር በርን በተመለከተ የታሪክ፣ የሕግ፣ የጂኦፓለቲካ እና ጂኦኢኮኖሚን መነሻ በማድረግ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር ዋነኛ ዓላማው መኾኑን አንስተዋል።
የተገኙ መረጃዎችን በመጠቀም የፖሊሲ ግብዓት የሚኾኑ ጥናቶችን ማዘጋጀት፣ ምሁራን እና ሲቪል ማኅበረሰቦችን በማሳተፍ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚቻልም ተነስቷል።
ይህ ፎረም ሀገራዊ አንድነትን እና ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም በምሁራን የሚደገፍ ጠንካራ መሠረት ለመጣል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም በመግለጫው ተነስቷል።
መድረኩ በሕግ፣ በምርምር እና በሙያዊ ድንበር ላይ ተመስርቶ ለቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሰላማዊ እና ሕጋዊ መፍትሄዎችን ለማበረታታት የተቋቋመ ነጻ ሙያዊ መድረክ መኾኑም ተነስቷል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#አዲስ_አበባ #ኅዳር_03_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ሃናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
