
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2019 ዓ.ም (አሚኮ) በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ አሳሳች መረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሥጋት ደቅነዋል። አጥፊ አካላት የሰዎችን ስሜት በመቀስቀስ ማኅበራዊ መከፋፈልን እና የፖለቲካ ውዥንብርን ለማስፋፋት ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙበት ነው።
የዓለም ኢኮኖሚ መድረክ (World Economic Forum) ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች በሕዝብ እና በተቋማት መካከል ያለውን እምነት ያጠፋሉ፤ ዴሞክራሲንም ያናጋሉ።
በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሠሩ ምስሎች እና ድምፆች (Deepfakes) ከእውነተኛው ለመለየት በሚያዳግት መልኩ እየተራቀቁ መጥተዋል።
ይህም እውነትን ከሀሰት ለመለየት አስቸጋሪ ማድረጉ ብቻ ሳይኾን አጥፊዎች እውነተኛ ማስረጃዎችን “በAI የተሠራ ነው” በማለት ተጠያቂነትን እንዲያመልጡ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
ይህ አደጋ በቴክኖሎጂ ገና በጅምር ደረጃ ላይ ባሉ ሀገራት ደግሞ የከፋ እና የጎላ ነው። በእነዚህ ሀገራት አብዛኛው ሕዝብ በስልኩ ያየውን ምስል ወይም የሰማውን ድምጽ በቀላሉ የእውነት አድርጎ ስለሚቀበል ለመታለል ቅርብ ነው።
በተጨማሪም ሀሰተኛ መረጃዎችን በፍጥነት አጣርተው የሚያወጡ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እና አሠራሮች በበቂ ኹኔታ አልተዘረጉም። ይባስ ብሎ ሀገራቱ ቀድሞውኑ የፖለቲካ ወይም የብሔር ውጥረት የሚበዛባቸው በመኾናቸው፣ በAI የተሠራ አንድ አሳሳች ምስል በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ብጥብጥ እና የደም መፋሰስ ሊያስከትል ይችላል።
በአጠቃላይ በእነዚህ ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የልማት መሳሪያ ከመኾን ይልቅ የጥፋት መሳሪያ የመኾን ሥጋቱ ከፍተኛ ነው።
ይህንን አደጋ ለመመከት ተቋሙ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አመላክቷል። ከእነዚህም መካከል የምስሎችን እና የዘገባዎችን ትክክለኛነት በዲጂታል ማረጋገጫ መሳሪያዎች መመርመር፣ ሕዝቡ የመረጃዎችን ምንጭ እና ዓላማ በጥንቃቄ እንዲመረምር ግንዛቤውን ማሳደግን መክሯል።
እንዲኹም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሠሩ ይዘቶች በግልጽ ተለይተው እንዲቀመጡ የሚያስገድዱ ሕጎችን መተግበር ተጠቃሽ ናቸው።
በአጠቃላይ አደጋውን ለመከላከል የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ብቻ ሳይኾን የሕግ እና የማኅበረሰብ ዝግጁነትም አስፈላጊ ነው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
