
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፦ ሠንደቅ ዓላማችን የመደመር ዕሴታችን፣ የአንድነታችንና የኢትዮጵያ ከፍታ ምልክታችን ነው!
ዛሬ 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አክብረናል! ሠንደቅ ዓላማ የቀደምት አባቶቻችንን የመሥዋዕትነት ታሪክ የሚያስታውሰን፣ የዛሬ ትጋታችንን የሚያንፀባርቅና የነገውን የብልፅግና ራዕያችንን የሚያመላክት የሀገራችን የከፍታ ዓርማ ነው።
የመደመር መንግሥት ዋነኛ ትኩረት ኢትዮጵያን በአንድነት፣ በሰላም፣ በልማትና በሁለንተናዊ ብልጽግና ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር ነው።
ሠንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ እንጂ የልዩነታችን ምንጭ መሆን የለበትም። በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት የተለያየን ብንሆንም፣ በኢትዮጵያዊነታችንና በጋራ የልማት ራዕያችን አንድ ነን።
የመደመር ዕሳቤም ልዩነቶቻችንን እንደ ሀብት በመቁጠር፣ የጋራ ዕሴቶቻችንን በማጠናከርና በትብብር የሀገራችንን ታላቅነት በተግባር ለማረጋገጥ ያነሳሳናል።
በዚህ ታላቅ ብሔራዊ ቀን፣ ሠንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገን እያውለበለብን ለአንድነታችን፣ ለሰላማችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለሀገራችን ብልጽግና ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር እናረጋግጥ።
እንኳን 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሰላም አደረሰን!
