
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመርሐ ግብሩ በመገኘት መልዕክት አሥተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የአንድነት እና የሉዓላዊነት ክብራችን ኀያል መገለጫ በኾነው ሠንደቅ ዓላማ ሥር ተሠባሥበን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል ለምናከብረው ቀን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር፣ ክብር እና ቃል ኪዳን በልቡ የሚያድስበት፣ ኅብረ ብሔራዊነት የተላበሰ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጋራ የምናጎለብትበት እና የነገውን ብሩህ ተስፋ የምናበረታበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን መኾኑን ተናግረዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ ኅብረት እና አንድነት ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅር፣ የብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ ትሥሥር እና የሥነ ልቦና አንድነታችን ማጽኛ ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የመስዋዕትነት፣ የነጻነት፣ የሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት መለኪያ፣ የሕዝቦች እኩልነት እና የኅብረታችን ሕያው ምስክር መኾኑንም ተናግረዋል።
የ19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ የሚያደርገው ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አጠናቅቃ አዲስ የሕዝብ አደራ የተቀበለ መንግሥት በመሠረተችበት ማግሥት ድባብ ውስጥ ኾነን ነው ብለዋል።
የሕዝብ አደራ የተቀበላችሁ ተወካዮች የሠንደቅ ዓላማ ክብር እና ልዕልና የሚመጥን ሀገራዊ አገልግሎት የመስጠት ኀላፊነት አለባችሁ ነው ያሉት።
የሕዝብን ዕኩልነት የሚያረጋግጡ፣ ብዝኅነትን የሚያስከብሩ፣ ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጡ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን በመደንገግ የምታደርጉት ጥረት ለሀገር ሕልውና ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን በመላው ጥቁር ሕዝቦች እና አፍሪካውያን ዘንድ የነጻነት፤ የዕኩልነት እና የጽናት ተምሳሌትነት በመኾኑ በርካታ ሀገራት ቀለማቱን የነጻነታቸው ዓርማ አድርገው ወስደውታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የሕልውና ፈተናዎችን በሕዝቦቿ የተባበሩ ክንዶች በማለፍ በምግብ ራስን በመቻል፣ የደኅንነት እና የጸጥታ ዘርፎችን በማዘመን ከፍ ያለ ውጤት አስመዝግባለች ነው ያሉት።
ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ውጤታማ የሚኾኑት ብሔራዊ አንድነት እና አሥተማማኝ ሰላም ሲረጋገጥ መኾኑንም ተናግረዋል። ግጭት የጥፋት ጎዳና፣ ሰላም ደግሞ የልባሞች መንገድ በመኾኑ የነፍጥ አማራጭ የመረጡ ታጣቂዎች ሰላምን እንዲያስቀድሙም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ቀጥ ያለ በጎነት ያለው እንዲኾን የወሰነ ትውልድ መፍጠርም ተችሏል ነው ያሉት። በዚህም በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት እና ትብብር ላይ የተመሠረተውን ፍትሐዊ የባሕር በር የማግኘት እና የመጠቀም መብታችንን የሚያረጋግጥ፣ መንገዱም ሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና በሰጥቶ መቀበል መርኅ የታለመ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ኀይሎች የሀገር አለኝታ፣ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና እና የሉዓላዊነታችን ታማኝ ጠባቂዎቻችን ናችሁ ብለዋል።
የምትከፍሉት መስዋዕትነት በትውልድ ሁሉ ከበሬታ እና ሞገስን ያገኛልም ነው ያሉት። ለሠንደቅ ዓላማችን ክብር በጽናት በጋራ እንቆማለንም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
