
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት “ሠንደቅ ዓላማችን ለኅብረ ብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን ” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል። የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ሠንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነት፣ የሀገር መለያ አርማ፣ የሕዝብ የማንነት መግለጫ፣ የጋራ አርበኝነት ታሪክ መጻፊያ፣ የአንድ ሀገር ምልክት ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ብዝኀ ማንነት ባለበት ሀገር አንድ የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል። ሠንደቅ ዓላማ የትናንት የአባቶቻችን አርበኝነት እና የነገ ልጆቻችን የምናስተሳስርበት አርማችን ነውም ብለዋል። የሠንደቅ ዓላማን ቀን ማክበር የሀገርን ታሪክ ለዘመከር እና ከዛሬ ጋር አስተሳስሮ ለመምራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ለሀገር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እና የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እንደሚከበርም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሠነቀችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የጋራ መግባባት መፍጠር እና በአንድነት መጓዝ እንደሚገባም አንስተዋል። ከግጭት ለመውጣት እና የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ኋላቀር እሳቤዎችን ወደጎን በመተው ትናንት አባቶቻችን በደማቸው ያቆሟትን ሀገር እኛ በላባችን ልናቆማት ይገባል ነው ያሉት። ሠንደቅ ዓላማ የሚያግባባን፣ የአንድነታችን እና የሀገራችን ምልክት ነው ብለዋል።
ለሠንደቅ ዓላማ መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ እና ለከፈሉ ጀግኖች ዕውቅና በመስጠት አንድነትን ማጽናት እንደሚገባም አመላክተዋል። ሠንደቅ ዓላማችን ታሪክ የምናስተላልፍበት አርማችን ነው፣ ኢትዮጵያን እንደተከበረች ጠብቆ ለልጆች ማስረከብ ይገባል ነው ያሉት። ሁሉም በተሰማራበት መስክ ሁሉ አርበኛ መኾን እንደሚገባውም አመላክተዋል። ሀገራችን ሠንደቅ ዓላማን የሚያስከብርላት፣ ክብሯን የሚያስጠብቅላት ትፈልጋለችም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከፍ እንድትል መግባባትን መፍጠር፣ ለሠንደቅ ዓላማው ክብር እና ሞገስ መስጠት ይገባልም ብለዋል። ለሀገራችን ክብር በአንድነት መቆም አለብንም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
