
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት የሠንደቅ ዓላማ ቀንን አክብሯል።
የባሕርዳር ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ (ዶ.ር) ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት ዋነኛ መገለጫ በመኾኑ ከምንም በላይ የላቀ ክብር ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ከፍ ብሎ የሚውለበለበው ብሔራዊ ዓርማ በቀላሉ የተገኘ ሳይኾን ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ሕይወታቸውን ገብረው እና አጥንታቸውን ከስክሰው በክብር ያቆዩት ውድ አደራ መኾኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር እና ከጥቃት ለመከላከል በየግንባሩ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ዜጎች በአንድነት በመቆም አስፈላጊውን ደጀንነት እና አቅርቦት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።
ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እና እያንዳንዱ ዜጋ ሀገራዊ ክብሩን ለልጆቹ፣ ለቤተሰቡ፣ ለሠራተኞቹ የማስተማር እና የማስረጽ የጋራ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙ አስተያየት ሰጭዎች የሠንደቅ ዓላማ ቀን ተተኪው ትውልድ አንድነቱን አስቀጥሎ እንዲጓዝ እና ኅብረ ብሔራዊነትን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
