
19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት “ሠንደቅ ዓላማችን ለኅብረ ብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) አክብረን የምንሰቅለው፣ በክብርም ከፍ አድርገን የምንመለከተው ሠንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን፣ የሉዓላዊነታችን እና የክብራችን ዘላለማዊ አርማ ነው ብለዋል፡፡
ቀኑ ከቀለም እና ከቅርጽ የዘለለ የብዙ ትውልዶች የጋራ ትግል፣ የጀግንነት፣ የጽናት እና የድል ታሪክ የተጻፈበት ታላቅ በዓል መኾኑንም ገልጸዋል።
ሠንደቅ ዓላማችን አባቶቻችን ሀገርን ከወራሪ ጠላት ለመከላከል ሲሉ አጥንታቸውን ከከሰከሱበት፣ ደማቸውን ካፈሰሱበት እና ውድ ሕይወታቸውን ከሰጡበት ታላቅ መሠረታዊ የጋራ ሀገራዊ እሴታችን መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
“ሠንደቅ ዓላማችን ለኅብረ ብሔራዊ መግባባት እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው በዓሉ ልዩነቶችን በውበት አቻችሎ፣ በአንድ የሠንደቅ ዓላማ ጥላ ሥር በጋራ ለመቆም የሚጠራ ብሔራዊ ጥሪ መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የጋራ ቤት ናት ያሉት አሥተባባሪው ቋንቋችን፣ ባሕላችን እና እምነታችን ቢለያይም የታሪካችን፣ የነጻነታችን እና የተስፋችን ማሰሪያ አንድ ነው ብለዋል። ሠንደቅ ዓላማ አብሮነትን በግልጽ የሚያሳይ ሕያው ምልክት መኾኑንም ገልጸዋል።
የሠንደቅ ዓላማን ቀን ስናከብር ለሠንደቅ ዓላማችን አኩሪ መስዋዕትነት በመክፈል ነጻ እና ሩቅ አሻራ ያላት ሀገር ያስረከቡንን የጀግኖች አባቶቻችንን አደራ በታላቅ ክብር ልናስታውስ ይገባል ነው ያሉት። ሠንደቅ ዓላማችን የትናንት ታሪካችን ማሳያ ብቻ ሳይኾን የነገ የኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሰሪያም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከሠንደቅ ዓላማዋ ክብር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መኾኑንም ገልጸዋል። በዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከመላው ሀገሪቱ ተሠባሥበው፣ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በአንድ ዓላማ ተሰልፈው ቅኝ ገዥን አሸንፈዋል፡፡ ያ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው ጥቁር ሕዝብ እና ለነጻነት ለሚታገሉ ሁሉ የተስፋ ብርሃን ኾኗል ነው ያሉት። ይህ ታሪክ አንድነታችን ኀይላችን መኾኑን በተግባር ያስተማረን ነው ብለዋል።
ዛሬም እንደ ትናንቱ የሀገራችንን ክብር የምናስጠብቀው በአንድነት፣ በመተባበር እና በጋራ ዓላማ ስንቆም ነው፤ የጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት የሚያስታውሰን ነጻ ሀገር ማስረከብ ብቻ ሳይኾን ያንን ነጻነት ከነሙሉ ክብሩ ጠብቀን ማሳደግም የኛ ድርሻ መኾኑን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ እና የልማት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አንስተው የኢትዮጵያን ማንሰራራት ለማረጋገጥ የዕለት ተዕለት ሥራችን፣ ትጋታችን እና ርብርባችን ከሠንደቅ ዓላማችን መርሆዎች ጋር የተጣጣመ መኾን አለበት ነው ያሉት።
ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ማለት ሕግን ማክበር፣ የሌሎችን መብት ማክበር እና ለዜግነት ግዴታ ታማኝ መኾን ማለት ነው ብለዋል። ሰላምን መጠበቅ፣ ግጭትን በውይይት መፍታት እና ልዩነትን እንደ ሀብት መመልከትም የሠንደቅ ዓላማ ክብር መገለጫዎች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ የምናሳየው የሠንደቅ ዓላማ ክብር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ትልቁ የሀገር ፍቅር ትምህርት ነው ብለዋል። ሠንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያውያን የዘመናት አብሮነት፣ የጋራ እጣ ፈንታ እና የመተሳሰሪያ ገመድ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ዓድዋን ጨምሮ በታሪክ ውስጥ የተመዘገቡት ድሎች የተገኙት የሠንደቅ ዓላማን ክብር ከፍ አድርጎ በመጠበቅ መኾኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በሰማይ ሥር በክብር ከፍ ብሎ በሰላም፣ በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ እና በዕድገት እንዲጸና የሁላችንም የዕለት ተዕለት ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
