
በአፍሪካ ቀንድ የቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ እና ተጽዕኖዋ ላይ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ትገኛለች።
ሀገሪቱ የቀደመውን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ልዕልናዋን ወደ ስትራቴጂካዊ የኀይል ሚዛን በማስቀጠል በኩል የምታደርገው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን እየሳበ ይገኛል። ይህም በቀጣናዊ ትስስር፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በወታደራዊ ዘርፎች በተሠሩ ስልታዊ እርምጃዎች የታጀበ ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ትኩረቱ ትብብርን መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲ ነው። ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ባለብዙ ወገን ጥቅም እንዲያስገኝ የታሰበ ስትራቴጅክ ስልት ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገንብታ ወደ ሥራ በማስገባት የኤሌክትሪክ ኀይል ለጎረቤት ሀገራት አጋርታለች። ይህም የጎረቤት ሀገራትን ጭምር ዘላቂ የልማት ምሰሶ በማድረግ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጽዕኖዋን አጎልብቶላታል።
የባቡር እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ማያያዟ ሀገሪቱን በቀጣናው የንግድ እና የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግም ታሳቢ ያደረገ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር የሚያያዝ ግዙፍ ድልድይ በመኾኑ ለሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ትልቅ አቅም ኾኗል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መኾኗ በምዕራቡ እና በምሥራቁ ዓለም መካከል የሚኖረውን የዲፕሎማሲ ሚዛን እንድትጠብቅ አስችሏታል። አዳዲስ የኢንቨስትመንት እና የንግድ አማራጮችን እንድታገኝም ዕድል ፈጥሮላታል።
የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መኾኗ አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ከተማ እና የአፍሪካ የፖለቲካ ውሳኔዎች ማፍለቂያ እንድትኾን አስችሏታል።
አለመረጋጋት በሚታይባቸው ሀገራት ያበረከተችው የዓለም ዓቀፍ እና አህጉራዊ የሰላም ማስከበር ሚናዋም ከፍ ያለ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ተጽዕኖ እንዲኖራት አድርጓል።
የቀይ ባሕርን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ የባሕር ኀይል ግንባታዋን ማጠናከሯ፣ ዘላቂ የባሕር በር አማራጭ ለማግኘት የምታደርገው እንቅስቃሴ ተጽዕኖዋን ከፍ እያደረገላት ይገኛል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ያላት ተጽዕኖ እያደገ መምጣት ታሪካዊ መነሻዎችን ከአሁናዊ የጂኦፖለቲካ እውነታ ጋር በማቀናጀት የመጣ ውጤት ነው። በቀጣናዊ፣ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱን የወደፊት ዕድል በመወሰን ረገድ የራሷን ወሳኝ ሚና መጫወቷን እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በዓለም ላይ አጉልቶ ሊያሳይ በሚችል መልኩ የተቃኘ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫን ትኩረት ታደርጋለች። ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን እንሠራለን ብለዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመሥራት መርህን እንገፋበታለን ነው ያሉት። የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የቀጣናውን፣ የዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ እና የወደፊቱን የዓለም እጣፋንታ ያገናዘበ የመከላከያ ኀይል መገንባትም ቁልፍ ጉዳይ መኾኑን አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
