የነኳት ለታ ታፍራለች፤ ትዕግስቷ የፍርሃት አለመኾኑን በክንዷ ታሳያቸዋለች።

35
ኢትዮጵያውያን በደስታም ኾነ በሐዘን መተባበር እና መተዛዘንን፤ በሰውነት መከባበርን፤ በልዩነቶች መቻቻልን፣ ለፈጣሪ፣ ለሕሊና እና ለሕግ መገዛትን እሴት ያደረጉ ሕዝቦች ናቸው።
ኢትዮጵያም በሕዝቦቿ ልክ የተሰፋች፤ የሌሎችን ጥቅም እና ሉዓላዊነት የማትነካ፤ የራሷን ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብት አሳልፋ የማትሰጥ፤ ለሌሎች ሰላም ዋጋ የምትከፍል ለቀጣናው፣ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የልማት እና የሰላም አምባሳደር የኾነች ጥንታዊት ሀገር ናት።
ኾኖም የሰላም መሻቷን እና አብሮ የማደግ ጥሪዋን በጥርጣሬ የሚመለከቱ፤ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ መመለሷን በስጋት የሚያዩ ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠላቶች አሉባት። እነዚህ ኀይሎች ከኢትዮጵያ የወሰዱት ሐቅ አልያም የሚፈልጉት ሃብት ስላለ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዋን በበጎ የሚመለከቱበት ዐይን የላቸውም።
ለዚህ ማረጋገጫው ታሪካዊ ጠላት የኾነችው ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማስቆም ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ እሰጣ ገባ ነው።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አቋም ፍጹም ግልጽ ነበር፤ ቅሬታዎችን በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት እና በሰላማዊ ውይይት መፍታት። ይህ ስልታዊ ጥረቷ እውነቷን ለዓለም ሲገልጥ ግብጽን ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት አከናንቧታል።
ይህን የጋራ ተጠቃሚነት መርኅ ኢትዮጵያ በባሕር በር ጉዳይም በግልጽ ተግብረዋለች። ቀድሞ የራሷ የነበረን የባሕር በር ለማስመለስ ስትነሳ ዓላማ ያደረገችውም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ቀጣናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። ይህ የሚፈጸመውም ከኀይል አማራጭ ይልቅ በሰጥቶ መቀበል መርኅ መኾን አለበት በማለት የብዙዎችን በር አንኳኩታለች።
ኾኖም ሁለቱ ጠላቶች (ግብጽ እና ሻቢያ) ለእኩይ ዓላማ ተጣምረው ጥያቄዋን ወደ ጎን መግፋታቸው ሳያንስ የውስጥ ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን በመጠቀም የውስጥ አለመረጋጋት የመፍጠር ብሎም ድንበር ተሻግረው ትንኮሳዎችን መፈጸም መጀመራቸውን መንግሥት አስታውቋል።
ታዲያ ኢትዮጵያ እነዚህን ትንኮሳዎች በትዕግስት የምትከታተለው ለቀጣናው ሰላም ካላት ኀላፊነት እንጂ ከፍርሃት አይደለም። የጠላቶች ትንኮሳ ቀይ መስመር አልፎ ብሔራዊ ደኅንነቷን አደጋ ላይ የሚጥል የመሰላት ጊዜ ግን እንደ አራስ ነብር በመነሳት ሉዓላዊነቷን እንዴት እንደምታስከብር በተባበረ ክንዷ ጥግ ድረስ ታሳያቸዋለች።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የሁከት ኀይሎች በየጊዜው በሀገሪቱ ላይ የጋረጡትን ፈተና በትዕግስት፣ በስክነት፣ በብርታት እና በጠጠረ ኀይልም ጭምር ማምከን ተችሏል ነበር ያሉት።
የዚህን ምስጢር ሲያብራሩም “የታላቅ ሀገር እና የነባር ሥልጣኔ ባለቤት የኾነ ሕዝብ መገለጫው ሀገርን ማጽናት፣ ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ሰላሙን መጠበቅ በመኾኑ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው የዕድገት ጉዞዎች ያለምንም ማወላወል የሚከናወኑ መኾኑን ለዓለም ማኅበረሰብ በሥራችን እና በትጋታችን ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል። የኢትዮጵያዊነት እሳቤ በእያንዳንዱ የእንቅፋት ጋሬጣ የሚደናቀፍ ሳይኾን ታላቁን ሀገራዊ ርዕይ እና አቅም ከፍ አድርጎ በማየት ላይ ያተኮረ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከታሪካዊ ልዕልና እስከ ስትራቴጂካዊ የኀይል ሚዛን
Next articleበደም የከበረች ሠንደቅ፣ በመስዋዕትነት የጸናች ሀገር !