በደም የከበረች ሠንደቅ፣ በመስዋዕትነት የጸናች ሀገር !

14
ፍቅሯን ለመግለጽ ቃላቶች ያንሳሉ፤ ስለ ክብሯ ለመጻፍ ብዕሮች በቂ አይደሉም፤ ቃልን በተግባር፤ ፍቅርን በመስዋዕትነት ይገልጹታል፤ ስሟ ሲነሳ እንደ ርዕደ መሬት ሰውነታቸው በፍቅር ይንቀጠቀጣል፤ ሠንደቅ ዓላማዋን ሲመለከቱ በከፍታዋ ስትውለበለብ የፍቅር እንባን ያፈሳሉ።
ሠንደቅ ዓላማዋ ሲነካ እንደ ብረት ጠንክረው፤ እንደ ፍም ግለው፤ ግርማ ነበልባልን ተላብሠው፤ በብርቱ ክንዳቸው ሠንደቃቸውን የነካ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት ያሳርፉበታል።
ሠንደቃቸው የነጻነት ምልክት ነው፤ ከራሳቸው አልፎ ለአፍሪካ ጥቅር ሕዝቦች የነጻነት ዓርማ ነው። በየተራራ እና ሸንተረሩ በአንድነት ዘምተው ጠላትን ድባቅ ይመታሉ። ስለ ሠንደቃቸው ይዋደቃሉ።
ሠንደቅ ዓላማ ከዓርማነት ባሻገር የአብሮነታቸው፤ የአንድነታቸው፤ የማኅበራዊ እሴታቸው፤ የኅብረ ብሔራዊነት የፍቅር መገለጫቸው ነው።
በባዶ እግራቸው፤ በኋላ ቀር የጦር መሣሪያቸው፤ ባልተደራጀ መዋቅራቸው፤ በባሕላዊ መገናኛ መንገድ በአንድነት ቆመው ለሠንደቅ ዓላማቸው በመዋደቅ የዓድዋ ድልን ተቀናጅተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት፤ የጥቁር ሕዝቦች ምልክት እንድትኾን በመስዋዕትነታቸው ሠንደቅ ዓላማን ከፍ አድርገው አሳይተዋል። ለሀገር ፍቅር ለሠንደቅ፤ ዓላማ ታማኝነት ሲሉ በርካቶች እንደ ሰም ቀልጠዋል፤ ደማቸውን አፍሥሠው አጥንታቸውን ከሥክሠዋል፤ አካላቸውን አጉድለዋል።
ለሠንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ታማኝነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል፤ በተሠማሩበት የሙያ መስክ የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም፤ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስመዝገብ፤ ሀገርን ለመውረር የሚመጣን ጠላት በደጀንነት በመታገል በተግባር ይገልጹታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠንደቅ ዓላማ የሁሉም ነገር ገደብ መኾኑን ሲያሳውቅ በግጭት ውስጥ” በሠንደቅ ዓላማ አምላክ” እያለ ግጭትን ለማስቆም ይጥራል። ይህም ያልተጻፈ ሕግ ኾኖ በማኅበረሰቡ ዘንድ የእርቅ ምልክት ኾኗል።
ሠንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያውያን የሕይወት መስዋዕትነት የሚከበርበት በዕለታዊ የሕይወት ክያኔ ውስጥ ክብር የሚሰጠው የሕልውና ጉዳይ ነው። ማኅበረሰቡ የሠንደቅ ዓላማን መዝሙር በሚሰማበት ቦታ ሁሉ በጽናት በመቆም ክብሩን በየአደባባዩ ይገልጻል። ዛሬም ድረስ የሠንደቅ ዓላማ ፍቅር እና ለኢትዮጵያ የሚከፈለው መስዋዕትነት በልጆቿ ብርቱ ክንድ ጸንቶ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ሠንደቅ ዓላማችን የጋራ ታሪካችንን፣ ሉዓላዊነታችን እና በልዩነቶቻችን መካከል በጋራ የመቆም አቅማችንን የሚያስታውስ የብሔራዊ የአንድነታችን ምልክት ነው ብለዋል።
‎
በዓድዋ የሀገሪቱ ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ በመቆማቸው፣ በታላቅ ገድላቸው የዓለምን ትኩረት መሳብ ችለዋል።
አባቶቻችን በፈተናዎች ከመከፋፈል ይልቅ አንድነታቸውን አሳይተዋል። ይህ በጋራ የመቆም ጥሪ መቼም ቢኾን ተቋርጦ አያውቅም፤ እያንዳንዱም ትውልድ ለዚህ ጥሪ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ነው ያሉት።
ለሀገር መቆም ከትንንሽ የድፍረት እርምጃዎች ይጀምራል፤ ከራስ አልፎ ሰፊ ርዕይ ይዞ መሥራትንም ይጠይቃል። ያለፉት ትውልዶች ሀገሪቱን እንድንረከብ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ዛሬ በጋራ የምናጸናትን ሀገር ነው ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየነኳት ለታ ታፍራለች፤ ትዕግስቷ የፍርሃት አለመኾኑን በክንዷ ታሳያቸዋለች።
Next article“ጠላት ሰማይዋን ላይደፍረው፣ ምድሯንም ላይረግጠው የተዘጋጀ ጋሻ”