“ጠላት ሰማይዋን ላይደፍረው፣ ምድሯንም ላይረግጠው የተዘጋጀ ጋሻ”

8
“ክፉሽን ለማየት በፍጹም አልወድም፣
ልሙት ለሰዋልሽ፣ ሕይወት ከአንቺ አይበልጥም፣
ቀርጿል ታሪክሽን ሲመሰክር ድንጋይ፣
ማንነቴን ክጄ ለአንቺ አንሼ ብታይ፣
ከዕድሜ ከሕይወቴ ሰስቼ ብነሳሽ፣
ይራቀኝ ሰውነት፣ ይርገፍ እንደ ጤዛሽ…!
ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ይህንን ግጥም በዜማ ሲያሰናዳው በሠራዊቱ ልብ ውስጥ እንደ እሳት የሚነደውን እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ለመግለጽ ነበር። እውነትም ሠራዊቱ ለእናት ሀገሩ ክብር እና ነጻነት ሲል ሞትን እንደ ቀላል የጉዞ አጋጣሚ እንጂ እንደ ፍርሃት አይመለከተውም።
እናት ሀገሩን ሊዳፈር ለመጣ አልሞት ባይ ተጋዳይ ነው፤ አድራጊነት እና አሸናፊነት ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰው ተፈጥሯዊ በረከቱ ነው።
ጽናት ከነፍሱ የተዛመደ፣ የውጊያ ጥበብ ከደሙ የተዋሃደ፣ በጠላት ፕሮፖጋንዳ እና ዛቻ ልቡ የማይሸበር የብረት አሎሎ ነው፤! ለሰከንድ እንኳ ሳይዝል የጠላትን የጥፋት ቀመር አስቀድሞ በመተንተን ሀገራዊ ጋሻነቱን ያስመስክራል።
የሠራዊቱን ታዓምራዊ ጽናት እና ጀግንነት በውል የተረዱት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ደራሲያን ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ዳምጠው፤ ብዕር ቀርጸው ታሪኩን ሊከትቡት ተገድደዋል።
ደራሲ ከበደ ሚካኤል የኢትዮጵያ ወታደር ሞትን የማይፈራ፣ ለነጻነቱ እና ለክብሩ ሲል እራሱን መስዋዕት የሚያደርግ የጽናት ተራራ፣ የሉዓላዊነት አርማ አድርገው በሥራዎቻቸው ገልጸውታል።
የጣሊያን ወራሪ ጦር መሪ የነበሩት ማርሻል ፒዬትሮ ባዶሊዮ በበኩሉ “የኢትዮጵያ ወታደሮች አስደናቂ ጀግኖች ናቸው፤ የመሣሪያ የበላይነት ባይኖራቸውም፣ የእኛን የጦር መሳሪያ እና ቦምብ ሳይፈሩ እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ ድረስ የሚዋጉ ቁርጠኞች ናቸው” በማለት እውነቱን ተናግሯል።
የሀገር ውስጥ አርቲስቶችም ቢኾን ስለ ሠራዊቱ ጀግንነት አንጎራጉረዋል። ይህ እና መሰል በብዕር እና በዜማ የተከተቡ የታሪክ ድርሳናት አንድ እውነትን ያስመሰክራሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያዊነት ማህተም፤ የሉዓላዊነታችን እና የሰላማችን ዋስትና ነው።
ይህ ሠራዊት ትላንት በየአውደ ውጊያው ድልን እየተቀዳጀ የመጣ የጀግንነት ውቅያኖስ ብቻ አይደለም፤ ዛሬም በዓለም አቀፍ እና በቀጣናው መድረክ ስሙ የገነነ፣ ተፈሪነቱ የጸና የሰላም ዋስ ኾኖ ቀጥሏል።
ከውስጥ ባንዳዎች እና ከውጭ ባዳዎች የሚሰነዘሩትን ሴራዎች በብቃት በማክሸፍ የዜጎችን ሰላም ሲያስጠብቅ ኖሯል። በዘመናዊ የውትድርና ሳይንስ ራሱን አሳድጓል፤ በረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅም ራሱን አዘምኗል።
“ሰማዩም ምድሩም የእኛ ነው!” በሚል ጽኑ መንፈስ በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። ጠላት ሰማይዋን ላይደፍረው ምድሯንም ላይረግጠው ከእናት ሀገሩ ጋር ቃል ኪዳን ተጋብቷል። ይህ ቃል ኪዳን የቃላት ድርድር ሳይኾን የሕይወት እና የሞት፣ የደም እና የአጥንት ፍቅር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም እና የአካባቢያችንን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ኃይል እንዲኖረን እንሠራለን ማለታቸው ይታወሳል።
በቀጣናችን የአየር የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ ትገነባለች። የሚኖረን መከላከያ ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁ እና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅም እና ቁመና ያለው ይኾናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበደም የከበረች ሠንደቅ፣ በመስዋዕትነት የጸናች ሀገር !
Next article“የሳይበር ደኅንነት የሀገር ደኅንነት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ