ጠላትን በሩቅ የሚያሥፈራው የሠራዊቱ ዘመናዊ የድሮን አቅም።

5
ክብሩ በሁሉም ኢትዮጵያ ልብ አርፏል፤ ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፍለው መስዋዕትነት እጅን በአፍ ላይ ያስጭናል፤ በእንቅስቃሴዎቹ ሁሉ የሕዝብን ፍላጎት እና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ያስቀድማል፤ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ይከሰክሳል፤ ለብሔራዊ ክብር በዋጋ የማይተመን ውድ ሕይወቱን ይገብራል የኢትዮጵያውያን የሀገር መከላከያ ሠራዊት።
በመንገዱ ሁሉ የሕዝብ ደጀንነት የማይለየው የመከላከያ ሠራዊትን ኀያል ክንዱን፣ ጀግንነቱን እና አይበገሬነቱን የሚያውቁ ጠላቶቹ ደግሞ በእጅጉ ይፈሩታል። ጦር እና ጋሻ ተጠቅመው በዓድዋ ተራራ ላይ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበሩ የጀግኖችን ታሪክ ደጋግሞ የሰማው፣ መስማት ብቻ ሳይኾን ደጋግሞ በየግንባሩ በድል አድራጊነት ያስቀጠለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጀግንነት እና ብልሃት ከዓድዋ ተምሮ ዛሬም በተጠንቀቅ ላይ ቁሟል።
በአባላት ቁጥር ብቻ ያልተወሰነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ አየር ኀይል፣ በስትራቴጂክ መረጃ አቅም፣ በዘመናዊ የትጥቅ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማፍለቅ ላይ የተመሠረተ ነው። ተቋሙ ዘመናዊ የአየር ክትትል፣ የራዳር ሥርዓቶች፣ የአየር መከላከያ አቅሞች እና የአውሮፕላን ጥገና አቅሙን አሳድጓል።
ዘመናዊ ድሮኖችን የታጠቀው የመከላከያ ሠራዊት ከንሥር በሚልቅ ፍጥነት እና በጥልቅ ዕይታ ጠላቶችን ወደ አመድነት ይቀይራል። የጦር እና ጋሻ ዘመን አብቅቶ ሰው አልባ ድሮኖችን፣ ተምዘግዛጊ ጀቶችን፣ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ተንጠልጣይ ድልድይ መኾን የሚችሉ የጦር መኪኖችን፣ መድፎችን፣ ታንኮችን እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሥሪያዎችን በበቂ ሁኔታ ታጥቋል።
ከሀገሩ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተወጣም ይገኛል። ጠላቶች ኢትዮጵያን ከመተንኮሳቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ዳር ድንበሯን ለመዳፈር የሚሞክሩ ታሪካዊ ጠላቶቿ ሠራዊቱን በሩቅ እንዲፈሩ አድርጓቸዋል።
ድሮን፤ ጥይት እና ሌሎች ለተቋሙ አስፈላጊ የኾኑ ግብዓቶችን በራስ አቅም በማምረት ተቋሙን አይደፈሬ ከማድረግ ባሻገር ለግዥ የሚወጣን የሀገር ሃብት እያዳነ ይገኛል።
የመከላካያ ሠራዊት የቴክኖሎጂ ግንባታ እና የታየው አስደናቂ ለውጥ የማረካቸው የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ከተቋሙ ጋር ለመሥራት ጥረት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ አየር ኀይል ምክትል አዛዥ ለከባድ ጥገና ማዕከል ብርጋዴል ጄኔራል መሠረት ጌታቸው በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ጠንካራ ተግባራት የኢትዮጵያ አየር ኀይል አቅሙን እንዲያሳድግ፣ ቴክኖሎጂን እንዲታጠቅ፣ ቴክኖሎጂን እንዲያለማ እና በላቀ ደረጃ እንዲተገብር አሥችሏል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)የውጊያ መልክ እየተቀየረ በመኾኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድሮኖችን በማምረት ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውን መደረጉን በአንድ ወቅት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የጦር ቴክኖሎጂዎችን ከመግዛት ወደ ማምረት መሸጋገሯንም ነው ያነሱት።
ድሮኖችን በስፋት በማምረት፣ በመረጃ፣ በማጥቃት፣ የጠላት እንቅስቃሴን ቀድሞ አውቆ ለማክሸፍም ወሳኝነት ያለው በመኾኑ ቴክኖሎጂን በራስ አቅም ለማምረት የተጀመረው ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ድሮኖችን ይበልጥ በማምረት በዓለም ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሠራች መኾኑን ተናግረዋል። ለድሮኖች የሚያገለግሉ ቦንቦችን በማምረት ላይ እንደምትገኝም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ አስተማማኝ አቅም መገንባቷን ገልጸዋል። ትናንሽ አቅም ይዘው ለሚሳሳቱ ኀይሎች ትንኮሳ ከማድረጋቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በስፋት እንደምትጠቀም ነው ያነሱት። ወታደራዊ አቅምን ይበልጥ ለማጠናከር አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን በማምረትም ውጤታማ መኾኗን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ28 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ኾነዋል።