በጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ28 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ኾነዋል።

4
በአማራ ክልል በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ28 ሚሊዮን 714 ሺህ በላይ ዜጎችን በጤና ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው የክረምት በጎ ፈቃድ መዝጊያ እና የበጋ በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በጎነት ባሕል እየኾነ መምጣቱን ጠቅሰው በከተማዋ ያለውን ሰፊ የወጣት ኀይል ለበጎ ፈቃድ ሥራዎች አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንደገለጹት በክረምቱ ነፃ የምርመራ፣ የቤት ለቤት ሕክምና፣ የቀዶ ሕክምና እና የወባ በሽታን የመቀነስ ሥራዎች በስኬት ተከናውነዋል።
አክለውም በቀጣይ የጤና አገልግሎት ጥራትን፣ ተደራሽነትን እና አይበገሬነትን ማረጋገጥ ትኩረት እንደሚሰጠውም ጠቁመዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው በክረምቱ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች 16 ሺህ ወሰን ተሻጋሪዎችን ጨምሮ በበጎ ፈቃድ ተሳታፊ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህ ወጣቶች የተቀናጀ እንቅስቃሴም የቤት እድሳት፣ የችግኝ ተከላ እና ማዕድ ማጋራት፤ የትምህርት ቁሳቁስ ማሠባሠብ እና የደም ልገሳ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት በጀት ማዳን የተቻለ ሲኾን በበጋውም ይህን ስኬት ለመድገም ዝግጅት መደረጉ ተጠቅሷል።
በጤናው ዘርፍ ብቻ በተከናወኑ ሥራዎች 4 ሚሊዮን 796 ሺህ 434 ተሳታፊዎች መሳተፋቸውን የቢሮው የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ምክትል ዳይሬክተር ሲስተር ሄለን ተሰማ ገልጸዋል።
ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴርን ወክለው በመድረኩ የተገኙት ዶክተር ሀብታሙ መንጌ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 166 ሺህ ከረጢት ደም መሠብሠቡን እና ከ28 ሺህ በላይ የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ሥራ በማስገባት የሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ እና የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኀላፊነታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።