11

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾን ሕዝብ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚጠበቀው አዲሱ የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል

በአማራ ክልል የጤና ሥርዓት ተደራሽነቱን ለማስፋት እና አገልግሎቱን ጥራት ያለው ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች እየተገነቡ ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ተጠቃሽ ነው። ይህ ጠቅላላ ሆስፒታል በ2009 ዓ.ም ነው የተጀመረው። አሁን ላይ የሆስፒታሉ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና መሠረተ ልማት ዳይሬክተር ደርባባው ሽፈራው የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱን ገልጸዋል።

​አሁን ላይ ግን የግንባታው አፈጻጸም 98 በመቶ መድረሱን እና ግንባታውን የመንቆረር ኮንስትራክሽን እያከናወነው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቀሩት የግቢ ውስጥ ውበት፣ ከውጭ የሚመጡ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማሟላት እና የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።

​ጠቅላላ ሆስፒታሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚኾን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የማይሰጡ አገልግሎቶችን በመስጠት ወደ ሌሎች ከተሞች ይላኩ የነበሩ ታካሚዎችን እንግልት እና ወጪ የሚቆጥብ ዘመናዊ ተቋም ነው ብለዋል። ​

ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲይዝ የሚደረገው እና በቅርብ ክትትል እየተደረገበት የሚገኘው ይህ ሆስፒታል በተያዘው 2019 ዓ.ም ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾን ነው የተናገሩት።

በመንቆረር ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ሙሉዓለም ብርሃን የሆስፒታሉ ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ተሥተጓጉሎ የቆየ ቢኾንም ኅዳር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን በጥራት በመገንባት ላይ መኾኑን ገልጸዋል። የቁሳቁስ ዋጋ ንረት ችግር እንደነበርም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የግንባታው አብዛኛው ተግባራትን በማከናወን አፈፃፀሙ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲኾን በርካታ ተግባራት መሠራታቸውንም ገልጸዋል።

የሆስፒታሉን ቀሪ ሥራዎች በማከናወን በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለማስረከብ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አምሳ አለቃ ታደለ አንተነህ የሆስፒታሉ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል። ጠቅላላ ሆስፒታሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት ሲጀምር ይፈጠርባቸው የነበረውን እንግልት የሚፈታ ነው ብለዋል። ተቋሙ በጉጉት የሚጠበቅ የመሠረተ ልማት መኾኑንም ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት ሲጀምር በዘመናዊ መሣሪያዎች ታግዞ ለአካባቢው ማኀበረሰብ ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ የሚያደርግ ተቋም መኾኑም ተመላክቷል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_01_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሃይማኖት፣ የጥበብ እና የተፈጥሮ መናገሻው ጣና ሐይቅ 🇪🇹