የሃይማኖት፣ የጥበብ እና የተፈጥሮ መናገሻው ጣና ሐይቅ 🇪🇹

5

 

ጣና ሐይቅ ውኃ ብቻ አይደለም፤ የሃይማኖት፣ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የመዝናኛ፣ የምርምር፣ የማረፊያ እና የተመስጦ ማዕከል ጭምር እንጂ። ጣና ሐይቅ ታሪክ፣ ሐይማኖት፣ ባሕል፣ ጥበብ እና ተፈጥሮ የተዋሃዱበት ድንቅ ሥፍራ ነው።

በውስጡ በያዛቸው የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች፣ ደሴቶች እና ጥንታዊ ገዳማት የጎብኝዎች ማዕከል እንዲኾን አድርጎታል። የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ያዘጋጀው የድንቅ ምድር አማራ መጽሐፍ መረጃ እንደሚያመለክተው በሐይቁ 37 ደሴቶች ይገኛሉ፡፡ ሐይቁ 45 ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የያዘ ድንቅ ሥፍራ ነው።

ሐይቁ የሥነ ምህዳር ሚዛንን ጠብቆ ተፈጥሮን እና ሰውን የሚያስማማ የፈጣሪ ገጸ በረከት ጭምር ነው።

በደሴቶች የሚገኙት ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የጥበብ፣ የዕውቀት፣ የፍልስፍና፣ የሥነ መለኮት እና የባሕል ማኅደር በመኾን ለዘመናት አገልግለዋል። ቅርሶችን ጠብቀውም ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

በውስጣቸውም አያሌ የብራና መጻሕፍት፣ የቀደምት ነገሥታት አልባሳት፣ የታሪክ እና የሃይማኖት መዛግብት፣ የሥነ ፈለክ እና የፍልስፍና ድርሳናትን ይዘዋል። ጥንታዊ የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ መስቀሎች፣ ጽናጽሎች፣ አክሊሎች እና ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳትም ተሰንደው ይገኛሉ።

የቀደምት ነገሥታት አጽም ያረፉበት ቦታም ነው። ለአብነትም አጼ ይኩኖ አምላክ፣ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ አጼ ዳዊት እና አጼ ፋሲለደስ በገዳማት አርፈዋል። የገዳማት ውጫዊ እና ውስጣዊ ክፍሎች በዘመኑ ሊቃውንት በተሳሉ ሃይማኖታዊ የግድግዳ ሥዕሎች እና በጥንታዊ ቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ያጌጡ ናቸው።

እነዚህ የጥበብ ውጤቶች የኢትዮጵያን የፊደል፣ የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና ጥልቀት እና የሳይንስ ልህቀት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ዛሬም ድረስ የጎብኝዎችን አዕምሮ የሚማርኩ፣ ትኩረትን የሚስቡ፣ የኢትዮጵያን የቀደመ ዕውቀት እና ጥበብ የሚመሰክሩ መገለጫዎችም ናቸው።

ዓባይ በጣና ላይ እንደ ሕያው ፍጡር የሚዋኝ መስሎ ሲያቋርጥ፣ ዓባይ ጣናን ተሰናብቶ ረጅሙን ጉዞውን የሚጀምርበት የደብረ ማርያም አካባቢ ለጎብኝዎች ሌላው አዲስ ክስተትን የሚፈጥር ነው።

የጣና ሐይቅ ገዳማት ከፍልቅልቋ እና ባለ ዘንባባዋ ባሕር ዳር፣ ከመናገሻዋ ከተማ ጎንደር፣ ከጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት እና ከጭስ ዓባይ ፏፏቴ ጋር ተሳስሮ ለኮፕ 32 እንግዶችም ዋነኛ መዳረሻ እንደሚኾን ይጠበቃል።

ጣና ሐይቅ ሁሉን እየሰጠ ጎብኝዎች መጥተው እንዲደነቁለት፣ እንዲማሩበት፣ እንዲዝናኑበት ሁልጊዜም ክፍት ነው። ከታናናሽ እስከ ግዙፍ የሐይቁ ጀልባዎችም እንደ ዘመኑ ዘምነው እንግዶችን ባሻቸው ቦታዎች ለማንሸራሸር ሁሌም ዝግጁ ናቸው።

‎#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_01_2019_ዓ_ም

✍️ በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከኮንትሮባንድ ስውር እጆች ወደ ቢሊዮን ዶላሮች ገቢ – የኢትዮጵያ ወርቅ የለውጥ ጉዞ 🇪🇹
Next article