ከኮንትሮባንድ ስውር እጆች ወደ ቢሊዮን ዶላሮች ገቢ – የኢትዮጵያ ወርቅ የለውጥ ጉዞ 🇪🇹

7

 

በእሳት ተፈትኖ የኢኮኖሚ ዋልታ ኾኗል፤ በጽናት ተጉዞ የውበት መድመቂያ ነው። የዓለም ገበያ ቁንጮ የጥራት መገለጫም ነው – የማዕድን ዘርፍ የስኬት በር የኾነው የወርቅ ሃብት።

ከዓመታት በፊት የወርቅ ምርት በባሕላዊ መንገድ የሚታፈስ፤ በኮንትሮባንድ ሥውር እጆች የተተበተበ ሀገር ረብ ያለው ጥቅም የማታገኝበት ማዕድን ሃብት ነበር። ዛሬ ግን ያ ምዕራፍ ተዘግቷል።

መንግሥት በሰጠው ትኩረት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወርቅ ግንባር ቀደም ተመራጭ ኾኗል።

ከሪፎርሙ በፊት ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ ምርት አነስተኛ ነበር። ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ እና የማዕድን ዘርፍ ሪፎርም በኋላ ግን ዓመታዊ ገቢ ላይ አወንታዊ ለውጦችን አስመዝግቧል።

ብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ተወዳዳሪ የግዥ ዋጋ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ እና ኮንትሮባንድ ላይ የተደረገው ቁጥጥር ለለውጡ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

የወርቅ ምርት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሠበሠብ በትኩረት ተሠርቷል። የሀገሪቱን ሃብቶች ከሀገር ውስጥ ማቀነባበሪያ፣ ከኢንዱስትሪ አቅም እና ከዘላቂ እሴት ፈጠራ ጋር ለማስተሳሰር የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጭ ኾነዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ወደ አገልግሎት መግባቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ የስኬት በር እንደሚከፍት ታምኖበታል።

ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ማዕድናትን የማጣራት አቅም እንዳለው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የወርቅ ጥራትን ለመለካት፣ ለማንጠር፣ ለውጭ ገበያ ዝግጁ ለማድረግ፣ በጥራት የተሰናዱ የወርቅ እና የብር ጡቦች ለማምረት ያግዛል። ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢን 80 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕድል እንደሚፈጥርም መረጃው ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ጥሬ እቃዎችን መላክ ቀንሳ እሴትን በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሠራች ነው ብለዋል። የማጣሪያ ፋብሪካው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን የምሥራቅ አፍሪካ እና አጠቃላይ የአፍሪካ ገበያን የማገልገል አቅም አለው ነው ያሉት።

መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እና ባከናወናቸው ተግባራት በ2018 በጀት ዓመት ሀገሪቱ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከወርቅ ምርት ማግኘት ችላለች ነው ያሉት።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_01_2019_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለውን የወባ በሽታ ለመግታት የሁለት ወራት የተቀናጀ የድንገተኛ ምላሽ ዘመቻ ሊጀመር ነው።
Next articleየሃይማኖት፣ የጥበብ እና የተፈጥሮ መናገሻው ጣና ሐይቅ 🇪🇹