
ወባ በቀላሉ ገዳይ በሽታ መኾኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያስታወቀው እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ የ610 ሺህ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን በመጠቆም ነው። ወባ የማኅበረሰብ የጤና ስጋት መኾኑ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በኢትዮጵያ በብዛት የሚስተዋሉት የወባ ዝርያዎች ፕላዝሞዲየም ፋልሲፈረም እና ቫይቫክስ መኾናቸውን በባሕር ዳር ከተማ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሃኪም ዶክተር አሰፋ መኳንንት ጠቁመዋል። ለዚህም ነው የበሽታው ዓይነት በምርመራ ሳይታወቅ መድኃኒቶችን መውሰድ ተገቢነት የሌለው እና አደገኛ ነው የሚባለው።
የአማራ ክልል ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንክር ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ ከሐምሌ ወር/2019 ዓ.ም ጀምሮ 400 ሺህ የወባ ሕሙማን ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። ስርጭቱ ከሳምንት ሳምንትም እየጨመረ ይገኛል።
አስተባባሪው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጓንጓ፣ ዚገም እና ቻግኒ፤ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ እንዲሁም በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የበሽታው ስርጭት ከፍ ብሎ መመዝገቡን አረጋግጠዋል።
ስርጭቱን ለመቆጣጠር በ17 ወረዳዎች የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መኾኑንም አስታውቀዋል። ሁሉም የጤና ተቋማት ሙቀት ያለባቸውን ሰዎች የወባ ምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በባሕር ዳር እና መሰል ከተሞች ለቤት ግንባታ የተሠሩ ሰው ሠራሽ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ለትንኝ መራቢያ እና ለበሽታ ስርጭት ምክንያት መኾናቸውን ጠቁመው ኅብረተሰቡ እና የግንባታ ባለቤቶች ግንባታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ባዶ በማድረግ ነዋሪውን ከአደጋ እንዲከላከሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንደጠቆሙት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለውን የወባ በሽታ ለመግታት የሁለት ወራት የተቀናጀ የድንገተኛ ምላሽ ዘመቻ ለመጀመር እየተሠራ መኾን ነው ያስገነዘቡት። የወባ ክስተት አሥተዳደር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን እና በየሳምንቱ አርብ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማጽዳት የጋራ ዘመቻ ይካሄዳልም ነው ያሉት።
በአጠቃላይ በሽታውን ለመከላከል የቆሙ ውኃዎችን ማፋሰስ፣ አጎበር መጠቀም፣ ፀረ-ትንኝ ኬሚካል መተግበር፣ ምልክቶች ሲታዩ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ መመርመር እና መታከም ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
