
የጎንደር ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዙር፣ 14ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ስለሺ መስፍን ባለፈው የበጀት ዓመት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤታማ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ሕዝብ እና መንግሥት የሰጧቸውን ኀላፊነት በአግባቡ በማይወጡ የሥራ ኀላፊዎች ላይ ምክር ቤቱ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ቁጥጥር እና ክትትል በትኩረት እንደሚያካሂድም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የ2019 የበጀት ዓመት ዕቅድን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በተያዘው የበጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸውን ዋና ዋና አቅጣጫዎች አብራርተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ተፈጥሯዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ይከናወናሉ።
በተለይም የኮሪደር ልማትን ማጠናከር እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋፋት እና የዲጂታል መታወቂያ ትግበራን ማፋጠን፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እና የከተማዋን ገቢ አሠባሠብ ማሻሻል፣ በግብርና ዘርፍ በመስኖ ልማት ከ433 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ማቀድ፣ በጤናው ዘርፍ የእናቶችን ጤና መጠበቅ እንዲሁም ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል መሥራት ከተያዙት ዋና ዋና ግቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ቆይታው በከተማው የጸጥታ ሁኔታ፣ በገቢ አሠባሠብ እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
