
ኢትዮጵያ የአንድ ቀለም ስዕል አይደለችም። ይልቁንም በተለያዩ ኅብረ-ቀለማት የተዋበች፣ በሺዎች በሚቆጠሩ የባሕል፣ የቋንቋ እና የታሪክ ፈትሎች የተሸመነች ድንቅ የጥበብ ሥራ እንጂ።
ኅብረ-ብሔራዊነታችን የተለያየ ኅብረ-ቀለም ያለው ነገር ግን በአንድ ጠንካራ የጋራ ቤት ስር የተገነባ የጽናት ማሰሪያችን ነው።
የሕዝቦቿ አንድነት፣ አልሸነፍም ባይነት፣ አይበገሬነት እና አይደፈሬነት በታሪክ ድርሳናት ደምቆ እና አሸብርቆ የተከተበላት ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በጽናት ታላቅ ጉዞዋን ቀጥላለች።
ይህ የማይናወጥ የኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የመገንባት ጉዞ የታላቅ ሕዝብ፣ የታላቅ ሀገር፣ ትልቅ ርዕይ ብቻ ሳይኾን የዛሬው ትውልድ ቃል ኪዳን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ተሳስረው፣ ተዋልደው እና ተጋምደው፣ ነግደው እና ተጋርተው፣ አርሰው እና አርብተው፣ ግጭቶችን እና ችግሮችን ፈትተው፣ ዳር ድንበራችንን በደም እና አጥንት አስከብረው፣ ክፉ እና ደግ ዘመናትን በአብሮነት አሳልፈዋል።
በዚያ ሁሉ ዘመን የጋራ ታሪክ እና የጋራ እሴት የገነቡት፣ ባሕል እና እምነት የተወራረሱት፣ ሥልጣኔን ተጋርተው የኖሩት በመደመር እሳቤ ስለተግባቡ ነበር።
ፈተናዎች ያልበገሩት፣ ችግሮች ያልበጠሱት፣ ርዕዮተ-ዓለሞች ያልቀየሩት፣ የውጭ ወረራዎች ያልሰበሩት፣ የፖለቲካ ሊሂቃን ያልከፋፈሉት ኢትዮጵያዊነት ሊገኝ የቻለው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንገድ ስለሚጓዙ ነው ብለዋል።
ሉዓላዊነት ድንበር ከመጠበቅ አልፎ የኢኮኖሚ፣ የምግብ ዋስትና እና የጅኦፖለቲካ ነጻነትን ያቀፈ ሁለንተናዊ እቅፍ ነው።
ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታስገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በበጋ መስኖ በማልማት ከራሷ የምግብ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ኤክስፖርት እያደረገች ትገኛለቾ።
ተፈጥሯዊ ሀብቷ በኾነው የዓባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጨት ችላለች። ይህም ለዘመናት በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የብርሃን አድማስ ያጎናጸፈ እና የኢኮኖሚ ነጻነቷን በተግባር ያረጋገጠ ትልቅ እርምጃ ነው።
ሀገሪቱ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን መብትን ማስከበሯ ደግሞ የሉዓላዊነቷ ጉዞ ዋና አካል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያውያንን ጽናት እና አይበገሬነት ሲገልጹ “በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ለማስከበር እና ግድባችንን ከፍጻሜ እንዳናደርስ በረጅም ገመድ አስረው ሲጎትቱን ተንገዳገድን እንጂ አልወደቅንም፤ በምግብ እና በወሳኝ ምርቶች ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን መውተርተር ሲሳለቁበት አንገት ደፍተን አልቀረንም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለአጎራባች ሀገራት በማካፈል አዲስ የዲፕሎማሲ መስክ ፈጥራለች።
ለጎረቤት ሀገራት (ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ) የኤሌክትሪክ ኀይል በመሸጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን እና የዲፕሎማሲ ጥንካሬን እያሳደገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የባሕር በር አማራጮችን ለማስፋት እና ቀጣናዊ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት እና የንግድ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ነው።
የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በዓለም ላይ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲቃኝ ይደረጋል፤ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር ብሔራዊ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን በትብብር የመሥራት መርሐችንን እንገፋበታለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር)።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊኾን አይችልምና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን ብለዋል።
ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የኀይላችን ምንጭ፤ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን ደግሞ የጽናታችን ማረጋገጫ ነው!
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
