የሕዝብ እና የሀገር ሰላም – የኢትዮጵያውያን የጋራ ኀላፊነት

12
ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ቁሳዊ ኪሳራ ከማድረሱም በላይ የበርካቶችን ሕይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል።
“ባልሽ ነው ገዳዩ፣ ወንድምሽ ነው ሟቹ” እንደሚባለው በጥቅሉ ችግሩ ያላንኳኳው በር፣ ያልደረሰበት ቤት የለም። ይህን ችግር ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት መንግሥት የሰላም በሩን ክፍት ማድረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የቀርበውን የሰላም ጦሪ የተቀበሉት በርካቶች ናቸው።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የቀድሞ ታጣቂዎች እንደሚሉት፤ በስሜት እና በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ በመግባት ሕዝቡን ሲበድሉ እንደነበር በጸጸት ይናገራሉ።
ከትክክለኛው የሰላም መንገድ መውጣታቸው ትልቅ ስህተት እንደነበር በመገንዘብ በትክክለኛው የህሊና ሚዛን ራሳቸውን በመመርመር ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን ነግረውናል።
​የቀድሞ ታጣቂዎች እንደሚሉት ባለፉት ጊዜያት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ በደልና እንግልት ሲያደርሱ እንደነበር ሳይሸሽጉ ያወሳሉ። በተለይም የሕዝብን ሰላማዊ እንቅስቃሴ አስተጓጉለዋል።
ይሁን እንጅ ጥፋትን በጥፋት ማረም ስለማይቻልና ላለፈው ስህተት ታላቁ ማካካሻ እውነተኛ ጸፀትና ወደ ሰላም መመለስ በመኾኑ፣ እነዚህ ዜጎች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው የሰለም አርማን አትመዋል። አሁን ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት በመምራት ላይ እንደሚገኙ በኩራት ይናገራሉ።
ከዚህም አልፈው አንዳንዶች ወደ መደበኛ የግል እና የመንግሥት የሥራ መስኮቻቸው በመመለስ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
መንግሥትም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሰማሩ እድሉን በማመቻቸት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያደረገ መኾኑ ይታወቃል። ይህ አበረታች እርምጃ የጦርነትና የግጭት ዋጋ ከንቱነትን የሚያሳይና የሰላምን ውድ ዋጋ የሚያረጋግጥ ህያው ምስክር ነው።
ሰላም የሁሉ ነገር መጀመሪያና የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው ያሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ ቀሪዎቹ ጓደኞቻቸውም የተዘረጋውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሕዝባቸው እንዲቀላቀሉ ምክረ ሀሳብ ለግሰዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል የመንግሥት ምሥረታ ባደረጉት ንግግር በክልሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ግጭቶች ካለፉ በኋላ የተገኘው ትምህርት “በጠላትነት እና በግጭት አሸናፊ አለመኖሩን ነው” ብለዋል።
ግጭት የዕድገት እና የመለወጥ ዕድሎችን የሚዘጋ፣ እናቶችን ለሀዘን የሚዳርግ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረትን የሚያፈርስ መኾኑን አንስተዋል። በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እና በዘላቂነት እንዲቆምም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በተለይም በጫካ ኾነው መሣሪያ ያነሱ አካላት የሕዝብን ሰላም ማስቀደም እንዳለባቸው እና ከሀገር ጠላቶች ጋር መተባበር በታሪክ ፊት የሚያዋርድ ተግባር መኾኑን ነው የጠቆሙት።
በውስጥ ቅሬታ እና ጥያቄዎች ቢኖሩም ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ብቻ እንደኾነ አስገንዝበዋል። የሰላም በሩ አሁንም ከፍት ነው ብለዋል።
የሰላምን አማራጭ በመከተል ለሕዝብና ለሀገር ግንባታ የየበኩልን አስተዋጽኦ ማበርከት የሁሉም ዜጋ የዜግነት ኀላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ የባሕር በር ሕልውና – የታሪክ፣ የሕግ እና የጂኦግራፊ እውነታ