ለቀጣናው ሰላም እና እድገት ዘብ የቆመችው ኢትዮጵያ

7
ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሁለንተናዊ ደኅንነት እና እድገት ተስፋ የሚጣልባት ሀገር ናት።
በዚህም ካላት ጂኦፖለቲካዊ ሚና አንጻር ፀጋዋን፣ የሕዝብ ብዛቷን እና የኢኮኖሚ አቅሟን ተጠቅማ የቀጣናውን ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በንግድ እና በሰላም ማስከበር ለማስተባበር ሰፊ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። አሁንም እያደረገች ትገኛለች።
የዓለም ባንክ ጥናቶች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግለጫዎች እና የሀገር ውስጥ የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ዘገባዎች እንደሚያመላክቱትም ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል የመኾን ራዕይ ሰንቃ በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ያመላክታሉ። የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የውህደት ጉዞ በሦስት ዋና ዋና የትስስር ዘርፎች የተከፈለ ነው። እያንዳንዱ ዘርፍ የራሱ የኾኑ ስኬቶች እና ዘላቂ ጥቅሞችም አሉት።
⚡️አንደኛው ዘርፍ ከኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ጋር የኤሌክትሪክ መስመሮችን በመዘርጋት ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች። ይህም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከማሳደጉም በላይ የጎረቤት ሀገራትን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ከፍተኛ የኾነ ዘላቂ ጥቅም ይሰጣል።
⛽️ በቅርቡ ከጅቡቲ እና ከኬንያ ጋር የተጀመሩት የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ እና የላሙ ወደብ-ደቡብ ሱዳን-ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ኮሪዶር (LAPSSET) ፕሮጀክቶችም አካባቢውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ለተወሰዱ ትልቅ እርምጃዎች ማሳያዎች ናቸው።
🚇 በሎጂስቲክስ እና ትራንስፖርት ዘርፍ የላሙ ኮሪዶር እና የተጣራ የነዳጅ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው። እነዚህ መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያ ተጨማሪ የወደብ አማራጮችን እንድታገኝ የሚያስችሏት ናቸው።
ለአካባቢው ሀገራት ደግሞ የታሪፍ እና የትራንስፖርት ወጪን በእጅጉ ይቀንሳሉ። ታዋቂው የፖለቲካ ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም የኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ቀጣናዊ ትስስርን ከወረቀት ወደ መሬት ያወረዱ ተግባራዊ የፖሊሲ ውጤቶች መኾናቸውን ይገልጻሉ።
🕊 ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የጸጥታ መረጋጋት እንዲኖር የነበራት እና አሁንም ያላት ሚና ከፍተኛ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ዘገባዎች እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ በሶማሊያ እና በሱዳን የተጫወተችው ሚና ለቀጣናው ሰላም መረጋገጥ መሠረት ኾኗል።
የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) ሲያደርግ በነበረው በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን የሰላም ድርድሮች ወቅት ኢትዮጵያ የተጫወተችው የላቀ ሚና በቀጣናው ወሳኝ እና አሥተባባሪ ሀገር መኾኗን ማሳያ ነው።
በሰላም እና ደኅንነት ዘርፍ ኢትዮጵያ በኢጋድ እና በአፍሪካ ኅብረት (AU) ጥላ ሥር በርካታ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በስኬት ተወጥታለች። ይህም ድንበር ተሻጋሪ ሽብርተኝነትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው። ለቀጣናው የኢንቨስትመንት ስጋትን በማስወገድ አስተማማኝ ምህዳር ይፈጥራል።
🎯 በጥቅሉ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚ እና በሰላም ማስተባበር ያላት ሚና ለቀጣናው ዘላቂ እድገት ወሳኝ ነው። የነዳጅ መስመር ዝርጋታዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እና የሰላም ማስከበር ሥራዎች ሀገሪቱ ለቀጣናው ውህደት የምትሰጠውን ትልቅ ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሕዝብ እና የሀገር ሰላም – የኢትዮጵያውያን የጋራ ኀላፊነት
Next articleለትልቅ ሀገር፣ ለትልቅ ሕዝብ እና ለታላቅ ርዕይ ዘመናዊ ወታደራዊ ቁመና ያለው ሠራዊት።