
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ቢኾንም መዘንጋት የሌለበት ትልቁ እውነት ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለው በታሪክ የእሷ የነበረውን መብት ነው።
ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ጸጋ ያጣችው በፖለቲካ ሸፍጥ እና የሀገሪቱ ሰፊ ሕዝብ ባልወሰነበት ዴሞክራሲያዊ ባልኾነ መንገድ ነው።
ዛሬም ቢሆን ሀገሪቱ ከቀይ ባሕር ዳርቻ ያላት ርቀት ከ30 ማይልስ በታች መኾኑ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ምን ያህል የማይነጣጠሉ እና የተቀራረቡ እንደኾኑ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ሕልውና ሙሉ ሊኾን የሚችለው አስተማማኝ የባሕር በር ሲኖራት ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የሕልውና መሠረቶች ናቸው በማለት ጉዳዩን በአንክሮ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ከቀይ ባሕር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መኾኑን በማስገንዘብ ጥያቄው የቅንጦት ሳይኾን የሕልውና መኾኑንን ጠቁመዋል።
የሕልውና ጥያቄው ከታሪካዊ እና ጂኦግራፊያዊ እውነታዎች ባሻገር በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍም የጸና ነው።
እ.ኤ.አ. በ1982 የጸደቀው የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ መብት አላቸው። በዚህ ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ወደብ አልባ ሀገራት ከባሕር ዳርቻ ሀገራት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት የባሕር በርን የመጠቀም መብት አላቸው።
የኢትዮጵያ ጥያቄ እና አካሄድም ከዚህ ሕጋዊ ማዕቀፍ ጋር ፍጹም የሚጣጣም ነው።
እነዚህ ሁሉ የታሪክ፣ የጂኦግራፊ እና የሕግ እውነታዎች ከጎኗ ቢኾኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የመጋፋት አሊያም በኀይል መሬት የመቀማት ዓላማ የላትም።
ኢትዮጵያ ይህንን የጂኦግራፊያዊ እስራት ለመፍታት እየተጓዘች ያለው በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ በተመሠረተ እና በሰላማዊ ውይይት ብቻ በሚፈጸም የዲፕሎማሲ መንገድ ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዞ ታሪካዊ ስህተትን በሰላማዊ መንገድ ለማረም የሚደረግ፣ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር እና የጋራ ብልጽግናን የሚያመጣ የላቀ የፖለቲካ ጥበብ ነው።
ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ ግዴታ እና የሕልውና ጥያቄ በጠረጴዛ ዙሪያ ተደራድሮ መፍታት ደግሞ የአሁኑ ትውልድ የማይታለፍ ኀላፊነት ነው።
#ባሕርዳር ጥቅምት01/2019 ዓ.ም
ስማቸው አጥናፍ
