
የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ ሲል በየበረሃው እና በየተራራው ምሽግ ይሠራል፤ እንደ መድፍ ምድርን ያንቀጠቅጣል፤ እንደ ንሥር ሰማይን ይቀዝፋል፤ የጠላትን የውጊያ ሰንሰለት በቅጽበት ይበጣጥሳል፤ የኮንክሪት ምሽግን ደርምሶ ድልን መቀዳጀት ልምዱ ነው።
ጽናት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ታማኝነት፣ ጀግንነት እና ጥልቅ የሕዝብ ወገንተኝነት የዚህ ኀይል የማይገፈፍ የክብር መገለጫዎቹ ናቸው።
እሱ የሚያየው የሀገርን ሕልውና ብቻ ነው፤ ክንዱ አይዝልም፣ ለሰከንድም አያንቀላፋም። በዐይኖቹ ውስጥ የሚታየው ቁርጠኝነት፣ በልቡ ውስጥ ያለው የጽናት እና የጀግንነት ወኔ፣ በክንዱ ያለው የሙያ ጥበብ እና ብቃት ኢትዮጵያ በጽኑ መሠረት ላይ እንድትቆም አድርጓታል።
በዚህ ድንቅ ጀግንነቱ እና አይበገሬነቱም ከቀጣናው አልፎ በዓለም የተመሰከረለት ደማቅ ዝናን ተላብሷል።
በዘመናዊ የጦርነት ጥበብ ውስጥ ከተለመደው የውጊያ መስመር ባሻገር በአንድ ቅጽበት የጠላትን ውሳኔ እና የውጊያ አቅጣጫ እንደ ማሽን የመቀየር አቅም ያለው የላቀ ኀይል መኖር የሀገር ሕልውና ጉዳይ ነው።
በዚህ ታላቅ ወታደራዊ አቅም ውስጥ ደግሞ እንደ አለት የፀናው እና የሀገር ደኅንነት አስተማማኝ ዘብ የኾነው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት “የልዩ ዘመቻዎች እዝ” በግንባር ቀደምትነት ይገኛል።
እዙ ለኢትዮጵያ ነፃነት እና ሉዓላዊነት መከበር መራር መስዋዕትነትን የከፈለ ባለ ውለታ እና የሀገር መከታ ነው።
የልዩ ዘመቻዎች እዝ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያሳየው እልህ አስጨራሽ ልምምድ፣ የረቀቀ የሥልጠና ሂደት እና በውጊያ ሜዳ ያስመዘገበው የማይናወጥ ስኬት ይህንኑ ዕውነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ይህ እዝ ያለፉት ዓመታት ድካም እና ልፋት ያፈራው የላቀ ሀገራዊ ሀብት ነው። የኢትዮጵያ የደኅንነት ዋስትና እና የማይበገር የጥንካሬ ማማ ኾኖ ቀጥሏል።
“የልዩ ዘመቻዎች እዝ” አባል መኾን ቀላል የሙያ ምርጫ አይደለም፤ ይልቁንም የሰው ልጅ የአካል፣ የሥነ-ልቦና እና የቁርጠኝነት ገደብ የሚፈተንበት የእሳት ዳራ ነው።
ጀግኖቹ በጥብቅ ሥነ ምግባር፣ በላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በከተማ እና በዱር ውጊያ፣ በፀረ-ሽብር ዘመቻዎች፣ ባልተጠበቁ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ፈጣን እና በሰከንድ የታለመ እርምጃ የመውሰድ ክህሎትን ተላብሰዋል።
የአየር ንብረት እና መልከዓ-ምድር የሚፈጥሩትን ተደራራቢ ፈተና አልፈው “ከእኛ በፊት ሀገር!” በሚል ጽኑ እምነት የደመቁ የሀገር መከታዎች ናቸው።
ለዓመታት የተካሄደው የካበተ ሥልጠና እዙን ከመደበኛ የጦር ኀይል አልፎ ወደ ፈጣን፣ ውጤታማ እና አይገመቴ የውጊያ ማሽንነት አሸጋግሮታል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ስለ ልዩ ዘመቻዎች እዝ ግንባታ እና አቅም ሲናገሩ ልዩ ዘመቻዎች እዝ የሀገራችን የመጨረሻው የደኅንነት ምሽግ እና የስትራቴጂክ ብልጫችን መገለጫ ነው ብለዋል።
“የልዩ ዘመቻዎች እዝ” በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ እና በየትኛውም ቦታ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በከፍተኛ ጥራት እና በፍጥነት የመፈጸም የላቀ አቅም ያለው፣ ለጠላቶች አስደንግጦ የሚቀጣ፣ ለወዳጆች ደግሞ ሙሉ እፎይታ የሚሰጥ የሀገራችን ታላቅ አቅም ነው” ብለውታል።
የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎችን የውጊያ ዝግጁነት አስመልክተው ሲገልጹ የልዩ ዘመቻዎች እዝ መገንባት የመከላከያ ሠራዊቱን የውጊያ አቅም ወደ ላቀ ዘመናዊ ደረጃ ያሸጋገረ ትልቅ እርምጃ መኾኑን ገልጸዋል።
በልዩ ሁኔታ የሠለጠኑ፣ ጠንካራ ሥነ-ልቦና እና ከፍተኛ የውጊያ ታክቲክ ክህሎት ያላቸው እነዚህ ኀይሎች ሀገር ያጋጠማትን ማንኛውንም ውሥብሥብ የደኅንነት ስጋት በአጭር ጊዜ እና በትንሽ መስዋዕትነት የመቀልበስ ሙሉ ብቃት አላቸው ነው ያሉት።
በሰው ኀይል ጥራት፣ በሥልጠና ጥበብ እና በዘመናዊ ስትራቴጂ የበለፀገው ይህ እዝ የኢትዮጵያ የሰላም ዘበኛ እና የታላቅነቷ ማረጋገጫ ኾኖ ቀጥሏል። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጽናት እና በልዩ ዘመቻዎቿ አቅም ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
