ሐቅን መርህ በማድረግ ሉዓላዊነትን የመጠበቅ ተጋድሎ!

49

 

ኢትዮጵያ በየጊዜው የእድገት ቁልፉን ያገኘች ሲመስላቸው ያረጀ ያፈጀ ትርክታቸውን እየረጩ፤ የዶለዶመ ሰይፋቸውን ታጥቀው የሚነሱ ሀገራት አያጧትም።

እነዚህ አካላት አንድም የኢትዮጵያን ሐቅ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ የዘረፉ፤ አለበለዚያም የኢትዮጵያን ሃብት ያለ ከልካይ መጠቀም የሚፈልጉ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “በጥልቅ ስትራቴጂካዊ እይታ ላይ የተመሰረተ ዝግጅት ማድረግ ባለመቻሉ የእድገት እና የፖለቲካ መሰናክሎችን መሻገር ለዘመናት ፈተና ኾኖ ቆይቷል” ብለዋል። ታሪካዊ ጠላቶቿ ሁሌም የእድገቷ እንቅፋቶች መኾናቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ኀያልነቷ ከተመለሰች ሐቋን የማስመለሷ ነገር የማይቀር መኾኑን በውል የሚገነዘቡት እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከዓይናቸው እንዲርቅ አይፈልጉም። በትክክለኛው የእድገት ጎዳና ላይ የኾነች ሲመስላቸውም ሁልጊዜም እንቅፋት ለመፍጠር ሲጣጣሩ ታይተዋል።

“የኢትዮጵያ የእድገት እና የልማት ሂደት በየጊዜው ድንቃራ የኾኑ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመውታል” ነው ያሉት። ኾኖም ኢትዮጵያ የእነዚህን ደንቀራዎች የጂኦ ፓለቲካ ጫና ተቋቁማ የእድገት መስመሯን መያዝ ስላለባት ጸጋዎቿን ለይታ ለልማቷ ትኩረት ሰጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ እንደተናገሩት ታሪካዊ ጠላቶቿ የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ በየተገኘው የትግል ሜዳ ሁሉ እንደሞከሩ፤ ነገር ግን እንዳልቻሏት፤ እንደማይችሏትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቁማ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ የግብጽን ምኞት አምክናለች፤ የእድገቷ ጉዞ የማይቀለበስ መኾኑንም አሳይታለች።

ይህ የእድገት ጉዞዋ የተሟላ እንዲኾን በታሪካዊ ጠላቶቿ የተወሰዱ ሐቆቿ ሊመለሱ ግድ ስለኾነ አንድ ብሔራዊ ጥቅም ነድፋለች፤ እርሱም የባሕር በር ባለቤትነት ነው።

የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የተገፋችበት ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ የባሕር በር ባለቤትነት የእድገቷ እና የሥልጣኔዋ ዋነኛ ሞተር በመኾኑ ነው። ይህን በማድረግ ሂደት ሻዕቢያ የተባለ ታሪካዊ ጠላት ሚናው ከፍተኛ ነበር።

ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር በመመለስ የባሕር በር ባለቤት ለመኾን ቆርጣ ስትነሳ እነዚህ ኀይላት በጎሳ ለተደራጁ የውስጥ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ ሉዓላዊነቷን መዳፈር እና ሰላምን በማናጋት የሀገርን ልማት ማደናቀፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ኢትዮጵያ የታሪካዊ ጠላቶቿን ሁለንተናዊ ጫና ከቁብ ሳትቆጥር በአቋሟ ጸንታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ (ዶ.ር) “ድህነቷን ለሚሹ እድገቷን፣ ከታሪክ መሰረዟን ሲጠብቁ ታሪክ እየሠራች፤ በእመርታ ወደፊት ትቀጥላለች” ብለዋል።

በእርግጥም ሕዝባዊ ተልዕኮ አንግቦ በዘመናዊ መንገድ የተደራጀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝብን ደኅንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መኾኑ ምስክር ነው።

የመደመር_መንግሥት

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ፣ #ታላቅ_ርዕይ 🇪🇹🇪🇹

👉ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና ሰጠ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ።