በክልል ፍርድ ቤቶች በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የተቀራረበ ደረጃ እንዲኖር ተሠርቷል።

13

 

ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ የፌዴራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል። ፕሬዝዳንቶቹ በሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የጋራ የለውጥ ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው።

በውይይቱ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ጉባኤው የሚመራበትን ደንብ አውጥቶ ለዓመታት ሥራ ላይ ማዋሉን ተናግረዋል። ፍትሕ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ እሴት በመኾኑ የፍትሕ ተቋማት የተለያዩ ሚና ስለማይኖራቸው በቅንጅት ለመሥራት ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ጉባኤ መመሥረቱን ገልጸዋል።

በዘርፉ ለዲጂታላይዜሽን ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል። ተቋማት በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የተቀራረበ ደረጃ እንዲኖራቸው ተሠርቷል ነው ያሉት። ጉባኤው በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል የልምድ ልውውጥ እና የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠር አስችሏልም ብለዋል።

ሃብትን በጋራ መጠቀም ላይ በትኩረት መሠራቱንም ነው ያነሱት። ዲጂታላይዜሽንን በትኩረት በመፈጸም ባለ ጉዳዮች ባሉበት ቦታ ኾነው የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኙ አሥችሏል ነው ያሉት።

በአንድ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ቃለ መሐላ በሌሎች ተቋማትም ተቀባይነት እንዲያገኝ ተሠርቷል ነው ያሉት። ኢ ፋይሊንግ ላይ በትኩረት መሠራቱንም አንስተዋል። መድረኩ በርካታ የለውጥ ውጤቶችን ማምጣቱንም ጠቁመዋል።

ለሦሥት ዓመት የለውጥ ፍኖተ ካርታ በፍርድ ቤቶች ሲተገበር ቆይቷልም ነው ያሉት። ለሁሉም ክልሎች የሚጠቅም የለውጥ ፍኖተ ካርታን ለመተግበር ያለመ መድረክ መኾኑንም ገልጸዋል።

የተቀላጠፈ፤ ነጻነቱን የጠበቀ የዳኝነት አካል፤ ግልጽ፤ ተገማች፤ ተደራሽ እና ሥርዓት ያለው አገልግሎት እንዲኖር ያስችላልም ብለዋል። መድረኩ ጥንካሬ እና ድክመቶችን ለመለየት እና አዳዲስ ዕውቀቶችን ለማምጣት የሚያስችል ነውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው ከ2016 ጀምሮ የዳኝነት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተፈጻሚ ሲኾን መቆየቱን አስረድተዋል። በዚህም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨባጭ የኾኑ ለውጦችን አምጥቷል ብለዋል። ለውጡ ጉባኤው ባሕርዳር ላይ እንዲካሄድ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ ባለበት ኾኖ አገልግሎት እንዲያገኝ ዲጂታላይዜሽን በትኩረት ተተግብሯልም ነው ያሉት። ባለጉዳይ ባለበት ኾኖ ክርክሮችን እንዲያካሂድ፤ አቤቱታዎችን እና መዝገቦችን የሚከፍትበት፤ ጉዳዮችን የሚከታተልበት በርካታ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

መደበኛ ሥርዓቱን የበለጠ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችሏል ነው ያሉት።

በበርካታ ቀበሌዎች የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም በክልሉ ዘላቂ ሰላም እና የሕዝቦችን መልካም ግንኙነት ለማዳበር በእርቅ ጉዳዮች እንዲፈቱ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የለውጥ ሥራዎችን ተቋማዊ ባሕል በማድረግ ፤ ቀጣይነትን የማረጋገጥ እና አዳዲስ የለውጥ ሥርዓቶችን በማምጣት የዳኝነት አካሉን ድንበር ተሻጋሪ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቆጭቶ ገብረማርያም የለውጥ ፍኖተ ካርታው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ያሳደገ፤ የልምድ ልውውጥ ሥርዓትን የፈጠረ፤ ችግሮችን በጋራ መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ እና ቅንጅትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኦቱከና ኦዳ(ዶ.ር) የለውጥ ፍኖተ ካርታው የሕዝብን የፍትሕ ፍላጎት እንድናሳካ አግዞናል ነው ያሉት። የሌሎች ክልሎችን ተሞክሮ በመውሰድ የእኛን ክልል ተሞክሮ በማካፈል የሀገርን የፍትሕ ፍላጎት ለማሟላት ሠርተናልም ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎ባለ ጉዳዮች የፍትሕ አገልግሎትን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እያገኙ ነው።
Next articleየደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና ሰጠ።