
ሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች ውይይት በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ የፌዴራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ተገኝተዋል። ፕሬዝዳንቶቹ በሀገሪቱን ፍርድ ቤቶች የጋራ የለውጥ ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንዳሉት በቅርብ ዓመታት በሀገር ደረጃ በተጀመረው የኢትዮጵያ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ አማካኝነት የቀጣይ የሦሥት ዓመታት የሀገር የዳኝነት አገልግሎት፤ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች እና በተያያዥ የፌዴራል እና የክልል የፍትሕ አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ለመምከር እና አቅጣጫ ለማስቀመጥ በመገኘታችሁ ደስተኞች ነን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ የለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለችም ነው ያሉት። በአጠቃላይ በፍትሕ አሥተዳደር ዘርፍ እና በዳኝነት አካሉ ላይ የተጀመረው የለውጥ እና የትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ በጉልህ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች ከሚያደርጉት የተናጠል የለውጥ ሥራ ባሻገር ሁሉም በጋራ በሀገር አቀፍ የሕግ ተርጓሚዎች መድረክ በመገናኘት የልምድ ልውውጥ መደረጉ ድንበር የለሽ የፍትሕ አገልግሎትን የሚያሳድግ እና የሚያዘምን መኾኑንም ተናግረዋል።
መድረኩ እንደ ሀገር አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እና ለመገንባት የተጀመሩ ጥረቶችን የሚያሳልጥ መኾኑንም ተናግረዋል።
የተቀናጀ እና የተናበበ የዳኝነት አካል እንቅስቃሴ የሀገርን የፍትሕ አሥተዳደር እንቅስቃሴ ትርጉም ወዳለው የለውጥ ምዕራፍ የሚያሸጋግርም ነው ብለዋል።
የተመዘገቡ ለውጦች ተቋማዊ እና ዘላቂ ኾነው እንዲቀጥሉ ያደርጋልም ነው ያሉት።
ከፍትሕ አሥተዳደር አልፎ ለሕግ አውጭ እና አስፈጻሚ አካላት ቅንጅታዊ እና የተናበበ አሠራር ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራልም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ ተምሳሌታዊ የቅንጅት አሠራር ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ለውጤታማ ቅንጅት የበኩሉን ይወጣል ነው ያሉት።
የዳኝነት አገልግሎት ዘርፍ በአንድ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል። የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲከበሩ፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መሥተጋብሮች ጤናማ፣ ሰላማዊ እና አሥተማማኝ እንዲኾኑ፤ ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሥፋፋ፤ ሰላም እና ደኅንነት እንዲረጋገጥ አይተኬ ሚና ይወጣል ብለዋል።
የዳኝነት ነጻነት እና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ለፍትሕ ፈላጊ ማኅበረሰብ ከአድሎ የጸዳ፤ የተፋጠነ ጥራት ያለው ፍትሕ በመሰጠት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በመንግሥት አካላት መካከል የመመዘን እና የቁጥጥር ሥርዓትን በመገንባት የመንግሥትን ቅቡልነት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና ይወጣል። የዳኝነት የአገልግሎት አሠጣጥን ለማዘመን እና በመሠረታዊነት ለመለወጥ የጀመርነው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የኅብረተሰቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት በዲጂታላይዜሽን የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎት እየተሠጠ ይገኛልም ነው ያሉት።
ለሌሎች ተሞክሮ የሚኾን ተግባር እያከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለክልሉ ሕዝብ የሚመጥን እና ትሩፋቱ ለሀገር የሚተርፍ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ሀገራዊ የፍትሕ ሙዚዬምን፣ ሰላም እና የሕግ የበላይነት የልህቀት ማዕከልን፣ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከልን እና በባሕርዳር ሁሉ አቀፍ የፍትሕ ማዕከልን ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቶች በቆይታቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና የባሕርዳር የልማት ሥራዎችን እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል። ባሕርዳር እና ክልሉ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
