‎🌾”እንደ ዘንድሮ ሰብል በቅሎ አያውቅም” አርሶ አደር

8

‎
‎
‎በአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን የተከናወኑ የግብርና ተግባራት፣ የቀረቡ ግብዓቶች እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤት አሳይተው የሰብል ቁመናው እጅግ ተስፋ ሰጭ ደረጃ ላይ ይገኛል።
‎
‎በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶ ሊበን ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ዓለማየሁ ፈቃዱ «እንደ ዘንድሮ ሰብል በቅሎ አያውቅም» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አርሶ አደሩ እንደገለጹት ከኾነ ይህ ውጤት የተገኘው ከእርሻ ዝግጅት እስከ አረም ማረም ያሉ ሥራዎችን በጥራት ከመሥራት ባለፈ የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ በመጠቀማቸው ነው።
‎
‎በአካባቢው ከጤፍ በተጨማሪ ስንዴ፣ ባቄላ እና ገብስ በስፋት የሚመረት ሲኾን በተለይም የጤፍ እና የስንዴ ማሳዎች ቁመና እና የፍሬ ሂደት አጥጋቢ በመኾኑ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ አብራርተዋል።
‎
‎የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ንጋቱ በዞኑ በምርት ዘመኑ 687 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 27 ነጥብ 06 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
‎
‎በዞኑ ስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ እና የቢራ ገብስን ጨምሮ 7 ዋና ዋና ሰብሎች 81 በመቶ የሚኾነውን የመሬት ሽፋን ይዘዋል ነው ያሉት።
‎
‎ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ የቀረበ ሲኾን የምርጥ ዘር አቅርቦትም ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።
‎
‎በበኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከ26 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በትራክተር መታረሱንም አመላክተዋል።
‎
‎ተባይ እና በሽታ እንዳይከሰት ሰብሉን በየጊዜው የማሰስ እና የመከላከል ሥራዎች በቅንጅት ስለመከናወኑም ነው ያብራሩት።
‎
‎በሌላ በኩል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንደገለጹት በምርት ዘመኑ በክልል ደረጃ ከ5 ሚሊዮን 5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም አስገንዝበዋል።
‎
‎ዶክተር ማንደፍሮ አዳዲስ የሰብል ሳይንሳዊ አሠራሮች፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የኩታ ገጠም እርሻ እና የቅርብ ክትትል በመደረጉ አብዛኛው ሰብል በአሁኑ ወቅት በአበባ እና ፍሬ በመሙላት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
‎
‎በምርት ዘመኑ የሚጠበቀውን የተትረፈረፈ ምርት በመሠብሠብ የክልሉን እና የሀገርን ኢኮኖሚ ከመገንባት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሰብል ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_30_2019_ዓ_ም
‎
‎ዘጋቢ፦ በሥራውድንቅ ደሳለው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሠራዊታችን የጦር ሰባቂዎችን ሕልም ማምከኑን ይቀጥላል” ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
Next articleአቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ኾነው ተሾሙ።