“ግጭት ይብቃ፤ ሰላም ይንገሥ🇪🇹

13

ግጭት የችግሮች መፍቻ መፍትሔ አይደለም። ይልቁንም የተጨማሪ ችግሮች መነሻ እንጂ። ይህንን በመገንዘብም በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ እና በግጭት ውስጥ ቆይተው ወደ ሰላም ጎዳና የተመለሱ ታጣቂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። የሰላም ጥሪውን መቀበላቸውም ለቀጣይ የክልሉ ዘላቂ ሰላም መሠረት እየጣለ ነው።

በተለያዩ ጊዚያት ሰላምን የመረጡ ታጣቂዎች በተለያየ ጊዜ ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት በግጭቱ ምክንያት የክልሉ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ በስቃይ እና እንግልት ውስጥ መቆየቱን መናገራቸው የሚታወስ ነው። ግጭቱ ሕይወት እና ሀብት እያሳጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ሕዝብ እየተጎዳ እና ልማት እየወደመ መዋጋት ትርጉም የለውም ብለዋል። ከእንግዲህ የትግል አቅጣጫችን ሕዝብን ከማፈናቀል እና ለርሃብ ከመዳረግ ይልቅ በሰላማዊ ውይይት መብቶችን ማስከበር ላይ ያተኮረ ይኾናል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የሰላም አማራጭ ሁልጊዜም ክፍት መኾኑን በተለያየ ጊዜያት ሲገልጹ መቆየታቸውም የሚታወስ ነው። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉ ወደ ሰላማዊ እና ሰብዓዊ አውድ እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። “የክልሉ መንግሥት የሰላም በሩን አሁንም ከፍቶ ይጠብቃል፤ የሰላም አማራጭን ለሚመርጡ ሁሉ ተገቢው ድጋፍ እና እንክብካቤ ይደረጋል” ብለዋል።

ለታጣቂዎች የተሰጠው ይህ ዕድል እና ታጣቂዎች እየወሰዱት ያለው እርምጃም በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ግጭቶች ሲቆሙ ዜጎች ከሥጋት ነጻ ወጥተው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እና ሥራቸው ይመለሳሉ።

በግጭት ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶች እንዲጠገኑ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንደገና እንዲያንሠራሩም እድል ይሰጣል። የኃይል እርምጃዎችን በማስቀረት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ብቻ የመፍታት ባሕልን ያጠናክራል። ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይትም በር ይከፍታል።

ታጣቂዎች የጦር መሣሪያዎቻቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላም ጎዳና መምጣታቸው ለአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ትልቅ እፎይታ ነው። የተጀመረውን ጥረት መደገፍ ደግሞ ከሁሉም ማኅበረሰብ ይጠበቃል።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_30-2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያን የኢነርጂ ታሪክ የሚቀይረው የኒውክሊዬር ፕሮጀክት!