‎”የኢትዮጵያ ጥንካሬ እና የማይበገረው ሕዝባዊ አንድነት”

25

‎
‎
‎የታሪክ ማህደር ገጾች ሲገለጡ የሀገራችን የኢትዮጵያ ስም በወርቃማ ቀለም ጎልቶ ከተጻፉ ጥቂት የዓለማችን ታላላቅ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ተቀምጦ እናየዋለን።
‎
‎ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ዘር መገኛ፣ የረጅም ዘመናት ረቂቅ ሥልጣኔ እና የጠንካራ መንግሥት ባለቤት ናት።
‎
‎በአፍሪካ ምድር የጥንታዊ ገናናነት፣ የኀያልነት እና የአይደፈሬነት ህያው ተምሳሌት የኾነችው ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ የማይበገር አብሮነት እና አርዓያነት ባለው አንድነትም ጎልታ ትታወቃለች።
‎
‎ለዘመናት በነጻነቷ እና በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጡ የጠላት ሴራዎችን እና የወረራ አደጋዎችን በመመከት በታሪክ ፊት የተመሠከረላት ሀገር ናት።
‎
‎ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “The Ethiopians” በተሰኘው ጥናታዊ ሥራቸው “ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ልዩ ቦታ ያላት ሀገር ናት፤ የራሷ ፊደል፣ ዘመን አቆጣጠር እና ጥንታዊ ሥልጣኔ ያላት፣ በቅኝ ግዛት ያልተደፈረች የታሪክ እና የነጻነት ምሰሶ ናት” ይላሉ።
‎
‎ምዕራባውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ተከፋፍለው በገዙበት እና አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በወደቁበት በዚያ ድቅድቅ ጨለማ የባርነት ዘመን ኢትዮጵያ የነጻነት እና የብርሃን ፋኖስ ኾና አብርታለች።
‎
‎የዓለም ኀያላን የነበሩትን ወራሪዎች በዓድዋ ተራሮች ላይ አይቀሬውን የምድር ውርደት ካቀመሰች በኋላ ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት ማስከበር ብቻ ሳይኾን ለፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና ለነጻነት ታጋዮች ትልቅ የመንፈስ ስንቅ ኾናለች።
‎
‎የበርካታ አፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት መውረሱም የዚሁ ታሪካዊ ኩራት ህያው ምስክር ነው።
‎
‎የሕዝቦቿ ጠንካራ ኅብረት እና የማያወላውል የሀገር ፍቅር ጋሻ ኾኖ ሀገርን ጠብቆ አቆይቷል።
‎
‎በኢትዮጵያ የታሪክ ጥናት እና ምርምር ውስጥ ታላቅ አሻራ ካሳረፉ አንጋፋ ምሁራን አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ድሌቦ «የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው “ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች የጋራ ቤት ናት፤ ሕዝቦቿ በጋራ በተከፈሉ መስዋዕትነት እና በባሕል ትስስር ሀገራዊ ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው አቆይተዋል” ሲሉ ያብራራሉ።
‎
‎በተመሳሳይ መልኩ ፕሮፌሰር ባሃሩ ዘውዴ “A History of Modern Ethiopia” በሚለው ሥራቸው “ኢትዮጵያውያን ከውጭ የሚመጣባቸውን አደጋ ለመመከት ያላቸው ዝግጁነት እና የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ሀገሪቱ በፈተናዎች ውስጥ እንኳ ሳትበገር እንድትቀጥል አድርጓታል” በማለት የታሪካችንን ምስጢር ይመሰክራሉ።
‎
‎ትናንት በኩራት የተጻፈው ታሪክ ዛሬም ይቀጥላል! አሁንም ቢኾን የኢትዮጵያን ዕድገት እና ጥንካሬ የማይሹ የውጭ ኀይሎች እና ከእነሱ ጋር የሚሰለፉ የውስጥ አፍራሽ አካላት የሀገራችንን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስደፈር እና ለማዳከም ቀን ከሌት ይደክማሉ።
‎
‎ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት እና ለሀገር ፍቅር የመቆም ጽናት ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ ይበልጥ የጸና ነው።
‎
‎ኢትዮጵያ በታሪኳ ለየትኛውም ወራሪ እና ተንኮል እጅ ሰጥታ አታውቅም፤ ዛሬም አትሰጥም! የውስጥ አንድነቷን በማጠናከር ብሔራዊ ጥቅሟን እና ነጻነቷን አስከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች።
‎
‎#የመደመር_መንግሥት!
‎#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
‎
‎ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
‎
‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_29_2019_ዓ_ም
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleታራሚዎች በይቅርታ እና በክስ መቋረጥ መፈታታቸው ከሰብዓዊ መብት አኳያ አወንታዊ ነው።
Next article“ሠራዊታችን የጦር ሰባቂዎችን ሕልም ማምከኑን ይቀጥላል” ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ