ለሰብል ሥብሠባ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል እንደሚፈልግ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

17

በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2018/2019 የምርት ዘመን ከ460 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ከ169 ሺህ 400 ሄክታር በላይ የሚኾነው መሬት በሰሊጥ ሰብል መሸፈኑን የተናገሩት የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጤናው ፈንታሁን ናቸው።

በዞኑ በባለሀብቶች እና በአርሶ አደሮች የለማው የሰሊጥ ሰብል አሁን ላይ መሠብሠብ መጀመሩንም አንስተዋል።
እስካሁንም በተደረገ ጥረት በዞኑ ከ48 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት የሰሊጥ ሰብል እንደተሠበሠበ ነው የተናገሩት።

ከለማው የሰሊጥ ሰብል ላይም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ ምርቱን ለመሠብሠብ በቂ የሠው ኃይል እንደሚጠይቅ ነው ያነሱት። አሁን ላይ የሰሊጥ ምርትን ብቻ ለመሠብሠብ 800 ሺህ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ የጉልበት ሠራተኛ እጥረት እያጋጠመ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይ አኩሪ አተርን ጨምሮ ሁሉንም የሰብል ዓይነቶች ለመሠብሠብ ዞኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

በዞኑ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ሰብል ውስጥ ከ12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

#የመደመር_መንግሥት

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ፣ #ታላቅ_ርዕይ 🇪🇹🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_29_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article‎”ዳኞች ከወገንተኝነት ነጻ የመኾን ተግባር ይጠበቅባቸዋል” የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት
Next articleታራሚዎች በይቅርታ እና በክስ መቋረጥ መፈታታቸው ከሰብዓዊ መብት አኳያ አወንታዊ ነው።