
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛው ዓመታዊ የዳኞች ጉባኤ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳዩ ያሉት መሻሻል እና ለውጥ ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል። ለውጡ ለምሳሌነት የሚቀርብ መኾኑን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች ተቀራራቢ በኾነ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እና ለዚህ የሚኾን ቁመና ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በትኩረት መሠራቱንም ገልጸዋል።
የክልል ፍርድ ቤቶች ከተደራሽነት፣ ከዲጃታላይዜሽን፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከቅልጥፍና እና አመቺ የሥራ ቦታ ከመፍጠር አንጻር የታዩ እመርታዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ይህ ውጤት የተገኘው በአመራር ቁርጠኝነት፣ የክልሉ መንግሥት በሰጠው ትኩረት እና በተባባሪ አካላት ድጋፍ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ የትብብር መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የተጀመሩት ሥራዎች ከነበርንበት አንጻር የተሻሉ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ልንደርስ ካለምነው አንጻር ብዙ ስለሚቀረን ቀሪውን ጉዞ በተባበረ ጥረት ልናጠናቅቅ ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ለዳኝነት አካሉ የሰጠውን ትኩረት እና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የዳኝነት አካላትም ትብብራችንን ማጠናከር አለብን ነው ያሉት። ዲጂታላይዜሽን የሕዝብ እርካታን እና የፍርድ ቤቶችን ታማኝነት የጨመረ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል። ዜጎች ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ዲጂታላይዜሽንን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
የዳኝነት አገልግሎት ከፍተኛ የሞራል ልዕልና የሚጠይቅ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሥነ ምግባር ሚዛኑ የተለየ፣ የሚጠበቅበት የባሕሪ ደረጃ ከፍ ያለ መኾኑን ተናግረዋል። ዳኝነት ፍላጎትን መስዋዕት በማድረግ ለመርሕ መቆምን የሚጠይቅ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዳኝነት ነጻነትን እና ገለልተኝነትን የሚፈልግ ተግባር መኾኑንም አንስተዋል። ዳኞች ሁሉንም በእኩል የማስተናገድ፣ ከወገንተኝነት ነጻ የመኾን እና በሕግ ላይ ብቻ ተመሥርቶ የመወሰን ተግባር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ለሕግ የበላይነት መጠበቅ እና ለፍትሕ መስፋት መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ዳኞች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት የሚወጡት ሙያዊ ብቃትን ይዘው ሲገኙ ነውም ብለዋል። ዳኞች አዳዲስ ሕጎችን ማወቅ እና አዳዲስ ክህሎትን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የዳኝነት ሥራ ፍትሕ የማስፈን ኀላፊነትን በዳኞች ላይ የሚጥል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኀላፊነታችን የገዘፈ እና ሀገር የሚቆምበት ነው ብለዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ለፍትሕ መስፈን በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_29_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
