
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛው ዓመታዊ የዳኞች ጉባኤ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው “የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ” በሚል መሪ መልዕክት ሲካሄድ የቆዬው ጉባኤ
ዳኞች የክልሉን ሕዝብ በላቀ ሥነ ምግባር እና የሙያ ብቃት ለማገልገል ያላቸውን ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ያሳዩበት መኾኑን ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያው ዓመታዊ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ የባሕር ዳር ቃል ኪዳንን ገብተን ተለያይተን ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዳኞች እና በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት መሪዎች የገቡትን ቃል በመጠበቃቸው የላቀ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
ጉባኤው ዳኞች የልምድ ልውውጥ ከማድረግ ባሻገር በቁልፍ የፍርድ ቤቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ የሚይዙበት፣ ተቀራራቢ አረዳድ እና መፍትሔ የሚያፈልቁበት፣ ሙያዊነትን የሚያጎለብቱበት ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከነበረበት ድባቴ ወጥቶ ሕገ መንግሥታዊ ቁመናውን በመያዝ በሕግም ኾነ በተግባር ሦሥተኛው የመንግሥት አካል መኾን ችሏል ነው ያሉት።
በሀገር ደረጃም በአርዓያነት ከሚጠቀሱ ተመሳሳይ ተቋማት መካከል ኾኗል ብለዋል። በተገኘው ውጤት ሳንኩራራ የዳኝነት አገልግሎትን በተሟላ መልኩ ተደራሽ እና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡ ለዳኝነት ሙያ ከሚሰጠው ከፍ ያለ ክብር በተቃራኒ በአንዳንድ ባለሙያዎች ላይ የሥነ ምግባር ችግሮች እንደሚስተዋሉ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ችግሩን ከመደበቅ ይልቅ በግልጽ ለመነጋገር ድፍረት ያስፈልጋል፤ ያንን ድፍረት ደግሞ በጋራ አሳይተናል ብለዋል።
ዳኝነት ከሕግ ዕውቀት ባሻገር የሕሊና፣ የሐቀኝነት እና የትሕትና ሙያ መኾኑን ገልጸዋል። ዳኛ በችሎት ውስጥም ከችሎት ውጭም ዳኛ ነው፤ የሕዝብ አመኔታ የሚገነባው በምንሰጠው ውሳኔ ብቻ ሳይኾን በምንኖረው ሕይወትም ጭምር መኾኑን ሁልጊዜም መዘንጋት የለብንም ብለዋል። በጉባኤው በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን እና ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
ፍትሕን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አንዱ የፍርድ ቤቶቻችን የትኩረት ማዕከል ኾኖ ይቀጥላልም ብለዋል። ሁሉም ክርክር በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ማለቅ የለበትም፤ በእርቅ እና በሽምግልና መፈታት የሚችለው ተፈቶ ፍትሕ ፈላጊውን ካልተገባ የጊዜ ብክነት እና ወጪ ማዳን ይገባል ብለዋል።
ከጉባኤው የምንወስደው ቁም ነገር ዕውቀት የማያቋርጥ ጉዞ መኾኑን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ
በፍጥነት በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ ኾነን አገልግሎት ስንሰጥ የትናንት ዕውቀታችን በወቅቱ የሚያጋጥመንን ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት በቂ አይኾኑም ነው ያሉት።
እንደ እኛ ያለ ከፍተኛ የሕዝብ አገልግሎት ኀላፊነት የወሰደ ሰው ያለማቋጥ ሙያን እያሳደጉ መሄድ ይጠበቅበታል ብለዋል። የዳኝነት ነጻነት እና ተጠያቂነት በእኩል ሚዛን ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል።
ዳኛ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ ኾኖ ሕግን እና ሕሊናውን ብቻ መከተል አለበት ነው ያሉት። በአንጻሩ በሂደቱ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ተጠያቂነትንም እያረጋገጡ መሄድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመዛግብት ውሳኔ አሰጣጥ ቅልጥፍና እየተሻሻለ ቢመጣም የዳኝነት አገልግሎት ጥራት በተለይም በወረዳ ፍርድ ቤቶች አሁንም ያልተሻገርነው ትልቅ ችግር ነው ብለዋል። ጥራቱ የተጠበቀ ውሳኔ በጊዜው ካልደረሰ ለተጎጂው ዋጋ ያጣል፤ በጊዜው የደረሰ ውሳኔም ጥራት ከሌለው ፍትሕ አይኾንም ነው ያሉት። ቅልጥፍና እና ጥራት አብረው መሄድ አለባቸው ብለዋል። የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ ተቋማዊ ቅርጽ ከያዘ በኋላ ያለክስ በማረሚያ ቤት ለነበሩ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ተችሏል ነው ያሉት። በጊዜ ቀጠሮ እና በዋስ አቤቱታዎች ላይ ይታዩ የነበሩ መገፋፋቶችም እየቀነሱ መጥተዋል ብለዋል።
ይህ መልካም ተሞክሮ በሁሉም ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት። ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ባሻገር የባሕል ፍርድ ቤቶችን እና ፍርድ ቤት መር አስማሚነትን ማጠናከር ፍትሕን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ውስጥ የተካተተውን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ድርሻ በአግባቡ ለመተግበር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችን ሁሉ ከተገበርናቸው የምንመኘው ተምሳሌት ፍርድ ቤት እውን ይኾናል ብለዋል።
አብዛኛውን ሕዝብ የሚያገኙት የወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞችም የውሳኔ ጥራታቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።
ጉባኤተኞች ወደየ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ የማኅበረሰቡን አመኔታ በሚያረጋግጥ መልኩ የዳኝነት ሥራቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
መዛግብት ያለበቂ ምክንያት እንዳይጓተቱ ክትትል እንዲያደርጉ፣ የቀጠሮ አሰጣጥ ፖሊሲ ሥርዓትን በጥብቅ ሥነ ምግባር እንዲተገብሩ እና ጥራት ያለው የፍርድ አጻጻፍ ልምድን እንዲያዳብሩ አሳስበዋል። የአንድ ዳኛ ስህተት የሁሉንም ዳኛ ስም ያጎድፋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ ከፍርድ ቤቶች ብዙ ይጠብቃል፡፡ ፍትሕ ፈላጊው ኅብረተሰብ ዳኞችን እንደ ሕግ ተርጓሚ ብቻ ሳይኾን እንደ ሰላም እና ፍትሕ ዋስትና ይመለከታቸዋል ብለዋል። ሰላም ያለ ፍትሕ አይጸናም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለእያንዳንዱ ዜጋ ተጨባጭ ፍትሕ በማቅረብ ለክልላችን ሰላም እና ልማት ማበርከት አለብን ብለዋል።
ራዕያችን ተምሳሌት የኾነ ፍርድ ቤት መገንባት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ ራዕይ በንግግር ብቻ አይሳካም፤ በእያንዳንዳችን የዕለት ተዕለት ውሳኔ፣ ሥነ-ምግባር እና የሥራ ትጋት ይገነባል ብለዋል።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_29_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
