
”ሥልጣን ኮፍያ ነው፤ ጭንቅላት አይደለም። ፀሐይ ካልበረታ ወይም አስፈላጊ ካልኾነ በማንኛውም ሰዓት ሊነሳ፣ በክብር ሊቀመጥ ወይም ሊወረወር ይችላል። አገልጋይ መኾን፤ እጃችንም፣ ልባችንም ንጹሕ መኾን አለበት።”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት ወቅት ሥልጣንን ከኮፍያ፣ ሰብዓዊ ማንነትን ደግሞ ከጭንቅላት ጋር በማነጻጸር የተናገሩት ይኸው መልዕክት አደራን ከማስጠንቀቂያ ጋር ያዋሀደ ነው።መሪዎች ከተሰጣቸው ኀላፊነት በላይ ራሳቸውን አግዝፈው
እንዳያዩ፣ ሥልጣን ውጫዊ እና ጊዜያዊ መለዋወጫ እንጂ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት ጋር አብሮ የተፈጠረ ዘላለማዊ ጸጋ አይደለም የሚለውን የሚያመሰጥር ነው። ኮፍያ ለፀሐይ መከላከያነት ወይም ለጌጥ እንደሚደረግ ሁሉ ሥልጣንም የሕዝብን ችግር ለመፍታት እና ሀገርን ለማገልገል
በጊዜያዊነት የሚሰጥ አደራ እንጂ መለያ ማንነት ሊኾን አይችልም። ”ፀሐይ ካልበረታ ወይም አስፈላጊ ካልኾነ በማንኛውም ሰዓት ሊነሳ ይችላል” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሹመት በወቅታዊ የሀገር እና የሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደኾነ የሚያሳይ ነው።
ሥልጣን መጥቶ የተቀመጠብን እንጂ አብሮን የተፈጠረ አለመኾኑን ማመን፣ ራስን ከተጠያቂነት እና ከሕዝብ የበላይነት በታች አድርጎ የማየት የትሕትና መገለጫ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መረዳት እንደሚቻለው ሥልጣን የሚቀጥልበት እና የሚለቀቅበት መንገድ የሚወሰነው
ኀላፊነቱን በያዘው ሰው የአገልግሎት ዘመን ተግባር መኾኑን ነው። ሕዝብን ያከበረ፣ ለሀገር የሠራ እና አደራውን የጠበቀ መሪ ኮፍያውን በክብር አስቀምጦ በታሪክ ገጽ ላይ በደማቁ ይጻፋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት በሚኒስትሮች እና በሚኒስትር ዴኤታዎች ላይ ጥብቅ ክትትል ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁንም ከፍተኛ ክትትል እንደሚደረግ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን ለግል ጥቅም እና ለጭቆና ያዋለ መሪ ከሥልጣኑ ይነሳል፤ ተጠያቂም ይኾናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እጃችንም፣ ልባችንም ንጹሕ መኾን አለበት” ብለዋል። ንጹሕ እጅ ከሙስና፣ ከስርቆት እና ከደም የጸዳን አሥተዳደር ሢመሠርት ንጹሕ ልብ ደግሞ ከቂም፣ ከጥላቻ እና ከክፋት የራቀ ቅንነትን ይገነባል።
ሥልጣን ኮፍያ መኾኑን የተረዳ መሪ ጊዜያዊ በኾነ ጌጥ ዘላለማዊ ማንነቱን አያሳድፍም። በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የአሥፈጻሚ
አካላት ዋነኛ ግባቸው ራስን ማግነን ሳይኾን በእውነተኛ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ፣ በንጹሕ ሕሊና እና በታማኝነት ሀገርን ማገልገል ብቻ መኾኑን ለትውልድ የሚሻገር የሞራል ዐምድ አድርጎ ያስቀምጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
