በሐረሪ ክልል ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተሠርተዋል።

4
በሐረሪ ክልል በ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች መካሄዳቸው ተገልጿል።
በክልሉ የ2018 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክም ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ እና የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አብዱልሐኪም አብዱማሊክ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱም ሰው ተኮር በኾኑ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች የበርካታ ዜጎችን የኑሮ ጫና ማቅለል የተቻለ ሲኾን ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቁመዋል።
የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤትን በቀጣዩ የበጋ ወቅት ይበልጥ ለማሳደግ በተቋማት እና በወረዳዎች ደረጃ የበጎ ሥራዎች ሚና መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የ2018 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ልዩ ረዳት ኃይለጊዮርጊስ መገርሳ በክረምቱ ወቅት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በዋናነትም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ውጤታማ የችግኝ ተከላ ማካሄድ መቻሉን ጠቁመው በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ፣ በመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እና ጥገናን ጨምሮ በትምህርት ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በጤናው መስክም ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ነፃ የሕክምና እና የጤና አገልግሎት መስጠት መቻሉን አመላክተዋል። በተጨማሪም በመሠረተ-ልማት ግንባታ፣ በትራንስፖርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በወጣቶች እና ሴቶች የሰላም እሴት ጥበቃ፣ በአቅመ-ደካሞች ቤት እድሳት እና በሌሎችም መስኮች የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ በክልሉ የተለያዩ ተቋማት እና የወረዳ መሪዎች ውይይት ያደረጉ ሲኾን በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
በሌላ በኩል በመድረኩ ላይ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ አሥተዳደር ቢሮ ኀላፊ ቶውፊቅ መሐመድ እና ከልዩ ልዩ ተቋማት የተውጣጡ መሪዎች የሰላም እሴትን ከማጠናከር አኳያ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ላይ ገለጻ አቅርበዋል።
በክልሉ ማኅበረሰቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተሠራው ሥራ አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን የጠቆሙት ኀላፊው፣ በቀጣይም የሰላም እሴት ግንባታን ይበልጥ በማጎልበት እና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎የጓዳ ኩርፊያ አላፊ ነው የሀገር ፍቅር ግን ሕያው ማሕተም ነው !
Next article“የኮፍያው ትርጉም በፖለቲካው መድረክ”