‎የጓዳ ኩርፊያ አላፊ ነው የሀገር ፍቅር ግን ሕያው ማሕተም ነው !

2
ኢትዮጵያዊያን የቀደምት የሀገር ፍቅር ታሪክ እና ሀገር የማስቀጠል ሂደትን በብዙ ሺህ ዘመናት ያጸኑ፤ በአብሮነት፣ በመስዋዕትነት እና በነጻነት ፍቅር የተገነቡ ናቸው። ሀገሪቱ የባዕዳን ወራሪዎችን ድል በማድረግ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፍ የቻለችው በሕዝቦቿ የጸና የሀገር ፍቅር ስሜት እና አንድነት ነው።
‎ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የክብር እና የሉዓላዊነት ምሽግ ኾና የዘለቀችው ልጆቿ ከልዩነቶች እና ከጊዜያዊ መከፋፈሎች ይልቅ የሀገርን ሕልውና ቅድሚያ በመስጠት ባሳዩት ታላቅ የዜግነት ቃልኪዳን ነው። በዚህም ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እና ታፍራ የምትኖር ገናና ሀገር ገንብተዋል።
የሀገር ፍቅር ማለት ልዩነቶችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ሳይኾን፣ የሀገር ጉዳይ ሲነሳ የነበረውን የውስጥ ጓዳ ኩርፊያ እና ቅሬታ ወደ ጎን በመተው ለአንድነት መሠለፍ ነው።‎​የውጭ ጠላት የሀገርን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት ሲደፍር፣ እነዚህ የቤት ውስጥ ውዝግቦች እንደ በረዶ ቀልጠው
ይጠፋሉ። በአንድነትም ይተማሉ። ሀገርም አጽንተዋል። ለሀገር ክብር ሲባል ብዙ ችግርም አልፈዋል።‎ልዩነት በአንድ የጋራ ኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ተበጅተው ሀገር የሚል ዜማ ይዘምራሉ። ሀገር በሚል ቃል ይታሠራሉ። ዛሬ የእኔ ኩርፊያ የሚቆየው ሀገር ከቀጠለች ብቻ ነው በሚል በአንድነት
የኅላፊነት ሥሜት ቅሬታዎችን ወደ ኋላ ይገፋሉ። ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ቅሬታዎች ተረስተው ሀገር የሚለው ስም ከፊታቸው ይደቀናል።ይህ
የሀገር ፍቅር መገለጫ በደም፣ በላብ እና በታላቅ ራስን ለሀገር በመስጠት የታነጸ ነው። አባቶቻችን ሕይወታቸውን ገብረው የሀገር ሉዓላዊነት
አስጠብቀው ታሪክን አሰናድተዋል። ይህም በፈተና ሰዓት አብሮ መቆም የኢትዮጵያዊነት ጽኑ መለያ መኾኑን በተግባር አሳይተዋል።‎ጠቅላይ
ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን ከፋም ለማም እንደ አንድ ተሳስረው፣ ተዋልደው
እና ተጋምደው፣ ግጭቶችን እና ችግሮችን ፈተው ኑረዋል ብለዋል። በተለይም የሀገሪቱን ዳር ድንበር በደም እና አጥንት አስከብረው፣ ክፉና ደግ
ዘመናትን በአብሮነት አሳልፈዋል ነው ያሉት። ይህም ብዝኅነትን ከአንድነት፣ የሃይማኖት ልዩነትን ከእሴት ትስስር፣ አካባቢነትን ከሀገር፣ የግል
ፍላጎትን ከቡድን፣ ትናንትናን ከዛሬ፣ አቅምን ከአቋም ደምረው ተጉዘዋል። እኛም ይህንኑ መንገድ መከተል ይገባል ብለዋል።‎​ዛሬም ቢኾን ሀገራችን
ከገጠሟት ፈተናዎች ለመሻገር የምታደርገው ጥረት የዚህን ታላቅ ታሪካዊ እሴት መድገም ያስፈልጋል ። የውስጥ ቅሬታዎችን በንግግር፣ በይቅርታ
እና በውይይት መፍታት፤ ከሁሉም በላይ ግን የሀገርን ሰላም እና ሉዓላዊነት ከማንም እና ከምንም በላይ ማስቀደም የዘመኑ የዜግነት ግዴታ ሊኾን
ይገባል።‎አንድነትን በማጽናት የጋራ ሀገር መገንባት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የዘለቀችው እና የምትቀጥለው በልጆቿ የጋራ ፍቅር፣ አንድነት እና
መሥዋዕትነት ነው። የውስጥ የጓዳ ኩርፊያ አላፊ ነው። ሀገር ግን ዘላለማዊ ናት።‎​ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያላት ሀገር ለትውልድ ማስረከብ ታሪካዊ ኀላፊነትም ሊኾን ይገባል።
‎
‎
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article‎ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሰኞ ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ይከበራል።
Next articleበሐረሪ ክልል ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ተሠርተዋል።