‎ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሰኞ ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ይከበራል።

6
‎የቀኑን አከባበር በማስመልከት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል፦ ‎19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የኢፌዴሪ መንግሥት ፕሬዘዳንት በተገኙበት በድምቀት ይከበራል፡፡
‎19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡
‎የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሠንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 (እንደተሻሻለው) አንቀጽ 2 መሠረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር ይደነግጋል፡፡ ‎ይህ በዓል ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበር እና ክብሯን ለማስጠበቅ ደምና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩት ሰንደቅ ዓላማ በጋራ የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር የመስጠትና የማክበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ ‎ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ በዋናነት የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫና አርማ ነው፡፡ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ ቀን የሚከበርበት ዋና ዓላማ ለሠንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበትና በሀገራዊ አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት መግባባትን የሚፈጥሩበት ሀገራዊ በዓል በመሆኑ ነው፡፡ ‎ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ከጀመረ እነሆ አስራ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ለአስራ ዘጠነኛ ጊዜ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነትና አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሀገራዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በድምቀትና በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ይከበራል፡፡
‎‎በዚህም መሠረት ክቡር የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዕለቱን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት በማስተላለፍ በንግግር ከከፈቱ በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት በመላው ሀገሪቱ ዜጎች በሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሃላ የሚፈጸምበት ሥነ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ‎‎ከዚያም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድ እና ክብር ዘብ ታጅበው በክቡር የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት አማካኝነት ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ይከናወናል። ‎‎በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ‎‎ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በተመሳሳይ ሰዓትና ድምቀት ይከበራል።
‎‎የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት!
‎
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር – የኢትዮጵያ የማይናወጥ ሉዓላዊነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ድል!
Next article‎የጓዳ ኩርፊያ አላፊ ነው የሀገር ፍቅር ግን ሕያው ማሕተም ነው !