ከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር – የኢትዮጵያ የማይናወጥ ሉዓላዊነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ድል!

8
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሃብቷን የመጠቀም መብት እና የባሕር በር ጥያቄ ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን የግብጽን ስሁት ሥነ ልቦና ከመሠረቱ አናግቶታል።
የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ በተሰኘው የጋዜጠኛ ስለአባት ማናየ መጽሐፍ ላይ ግብጽ አግላይ የኾኑትን የ1929 እና 1959 ስምምነቶችን ተገን በማድረግ ኢትዮጵያን የማዳከም እና የማተራመስ ቋሚ ስትራቴጂ ስትከተል ኖራለች።
የግብጽ ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን መኾን መሪር ሽንፈትን ቀምሷል። ግብጽ ግድቡን በኀይል ለማፍረስ እስከ መዛት ብትደርስም ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በጽናት ተሻግራ ግድቡን ለቀጣናው የኢኮኖሚ ምሰሶ በማድረግ የውኃ ላይ ሉዓላዊነቷን አረጋግጣለች።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ወደ ቀይ ባሕር ፊቱን ሲያዞር የግብጽ የህልውና ስጋት እጥፍ ድርብ ኾኗል። በአውሮፓ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አስተባባሪ ኤፍሬም ዘውዱ እንዳሉት ግብጽ የሕዳሴውን ግድብ ማስቆም ሲያቅታት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትወጣ በመስጋት ቀጣናውን ለማተራመስ ጥረት ላይ ናት።
ግብጽ ሕገ ወጡን የሕወሃትን ቡድን እና ሻዕቢያን ከምሥረታቸው ጀምሮ በመደገፍ እና ኤርትራን በማስገንጠል ኢትዮጵያን ከባሕር በር አርቃለች።
ዛሬም የሀገር ውስጥ አማጽያንን በማገዝ እና የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር በመውተርተር ዕኩይ ሤራዋን አጠናክራ ቀጥላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ቀይ ባሕር እና ዓባይ የኢትዮጵያ የህልውና መሠረቶች ናቸው፤ የባሕር በር የምንፈልገው በሰላም እና በሕግ አግባብ ነው” በማለት የሀገሪቱን ጽኑ አቋም አስገንዝበዋል።
ግብጽ የቱንም ያህል የጥፋት ሴራ ብትጎነጉንም ኢትዮጵያ አሻጥሮችን አክሽፋ የጀመረችውን የብልጽግና እና የሉዓላዊነት ጉዞ ማሳካቷ የማይቀር ዕውነታ ነው።
✍️በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛው ዓመታዊ የዳኞች ጉባኤ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
Next article‎ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሰኞ ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ይከበራል።